Annual summer camp gets underway
ዳንኤል ሆይ፣ አንተ ግን እስከፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመራመራሉ እውቀትም ይበዛል፡፡ ዳንኤል 12:4 ይህ ዘመን ከየትኛውም ያሳለፍናቸው ዘመናት በበለጠ የቴክኖሎጂ ዘመን መሆኑን ሁሉም ይስማማሉ። አንዳንዶች ከዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት አልፈው ሱሰኛ ለመሆን በቅተዋል። በዚህ አጭር መጣጥፍ ስለቴክኖሎጂ ትርጉምና ቴክኖሎጂ በትውልዱ ላይ (በተለይም በክርስቲያኖች ላይ) ስላለው ጥቅምና ጉዳት አይተን በጠቃሚ ምክሮች እንሰናበታለን።
ኤሌክትሮኒክስና ከመረጃ መረብ
ቴክኖሎጂ ወንጌልን ለፍጥረት ከማስፋፋትና አማኞችን እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ከማድረግ አንጻር ጎጂ ነው ወይስ ጠቃሚ የሚለውን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት፣ ቴክኖሎጂ ማለት ምን ማለት እንደሆነ መግባባት ያለብን ይመስለኛል። ቴክኖሎጂ ሲባል ቶሎ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው ኤሌክትሮኒክስ የሆኑ ነገሮች ቢሆኑም ቴክኖሎጂ የሚለው ትርጉም ሰዎች አንድን ስራ በተሻለና በተቀላጠፈ መንገድ ለመስራት የሚጠቀሙባቸውን የተለያዩ ዘዴዎች በሙሉ የሚያጠቃልል ዘርፈ ብዙ ነው። ለምሳሌ በጃችን ያለው ዘመናዊ ስልክ፣ የምንነዳው መኪና፣ በቤታችን የምንጠቀምበት ማሞቂያና እናቶቻችን የሚጠቀሙበት የእንጀራ ምጣድ ድረስ ሁሉም የቴክኖሎጂ ውጤቶች ናቸው። እነዚህን
የቴክኖሎጂ ውጤቶች ማንም በትክክል የሚያስብ ሰው በደፈናው ጎጂ ናቸው ብሎ ሊረግማቸው አይችልም። በአንድ መንገድ ይሁን በሌላ፣ ቴክኖሎጂ (ከዚህ በሁዋላ ኤልክትሮኒክስ የሆኑትን ማለቴ ነው) የሚሰጠን ጥቅም የማይካድ ቢሆንም አንዳንዶች ቴክኖሎጂ
ለክርስትናና ለመንፈሳዊ ህይወት እንቅፋት እንደሆነና መራቅ እንዳለብን ይናገራሉ። በዚህ ጽሁፍም ለማቅረብ የምሞክረው ስለጠቅላላ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሳይሆን ስለ ኤሌክትሮኒክስና ከመረጃ መረብ (ከዚህ በሁዋላ ኢንተርኔት እያልኩኝ የምጠራው) ጋር የተያያዘውን ቴክኖሎጂ ብቻ ነው። ቴክኖሎጂ ለክርስትና ችግር እንደሆነ የሚናገሩት ሰዎች ከሚያነሱት ሐሳብ መሀከል ባህልን ያበላሻል፣ ከሰዎች ጋር ያለንን ህብረትን ይቀንሳል፣ ልቅ ለሆነ የሞራል ውድቀትና ሐጢያታዊ ልምምድ ይዳርጋል፣ ልፍስፍስና ምድር ተኮር ክርስቲያን ያደርጋል የሚሉትና የመሳሰሉት ይገኙበታል።