አግድም አደጉ የእምነት እንቅስቃሴ አስተምህሮ

በሰባዎቹ መጨረሻ ጀምሮ የኮሪያዊው ሰባኪ የፖል ዮንጊ ቾ1 ስብከቶች በካሴት ተዘጋጅተው በአገሪቱ ውስጥ በስፋት ይሠራጩና ይደመጡ እንደ ነበር አስታውሳለሁ። በተለይ፣ “ዘ ፎርዝ ዳይሜንሽን” (“The Fourth Dimension, Vol.1 and Vol. 2”)2 በሚል ርእስ የታተሙት ሁለት ቅጽ መጻሕፍት፣ ብዙዎች እጹብ ድንቅ በማለት አሞካሽተውት ነበር3። ከሊቅ እስከ ደቂቅ በትምህርቱ ያልተደመመ፣ ከአምላክ ማደሪያ/ጸባኦት በቀጥታ የተቀዳ መገለጥ መሆኑን ያላጸደቀ ግለሰብ ያለ አይመስለኝም4። የዐቅብተ እምነት አገልግሎት ብቻ ሳይሆን፣ ነገረ መለኮትም በቅጡ በማይታወቅበት በዚያ ጨለማ ዘመን፣ አለማወቅን ተገን አድርጎ የተነሣው ይህ ትምህርት፣ አላንዳች ከልካይ እንደ ተዛማጅ በሽታ አገሪቱ ላይ ናኝቶአል፤ የቤተ ክርስቲያንንም አስተምህሮና ሥነ ምግባር ክፉኛ በርዟል።

ሞተ ሲባል ዐፈር እየላሰ የሚነሣው

ከመነሻው የብዙዎችን ልብ የሳበው ይህ ትምህርት፣ ከሱ በኋላ ለመጡት መሰል “የእምነት እንቅስቃሴ” ትምህርቶች5 ትልቅ የማደላደል ሥራ ሠርቷል። የእንቅስቃሴው ልሳን የነበረውና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ታትሞ በአገሪቱ ውስጥ በስፋት ይሠራጭ የነበረው “አክትስ” መጽሔት፣ለእንቅስቃሴው ማበብ ትልቅ ድርሻ ነበረው። ኋላ በእንቅስቃሴው አስተምህሮ የደቆኑ የናይጄሪያ ሰባኪያን ወደ አገሪቱ በስፋት በመግባት፣ በጽሑፍና በካሴት የተሠራጨውን መከር በጥቂት ወራት መሰብሰብ ችለዋል፡፡ ምናልባት ትምህርቱ ሞተ ሲባል ዐፈር እየላሰ የሚነሣው፣ ከተገመተው በላይ ሥር ስለሰደደ ይሆንን? እኔ በዚህ ጽሑፍ ይህ እንቅስቃሴ እምነትን አስመልክቶ የሚያስተምረውን ትምህርት እተቻለሁ።