ቤተክርስቲያንና የመንግሥት ፍትሐዊ አገዛዝ ተኣማኒነት
Dr. Girma Bekele, Seattle WA USA
በድጋሚ ላሳስብ፤ እግዚአብሔር መንግሥታትን የሚያስቀምጠው፣ የእርሱ የጽድቅ፣ የፍትሕና የምሕረት አገዛዝ አስፈጻሚ እንዲሆኑ ነው። የአገዛዛቸው ፍትሓዊ ተኣማኒነት ልኬቱ ይኸው እውነት ነው። ቃሉ እንደሚል፣ “ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፤ ገዦችም ትክክል የሆነውን ሕግ ይደነግጋሉ፤ መሳፍንት በእኔ ይገዛሉ፤ በምድር ላይ የሚገዙ መኳንንትም ሁሉ በእኔ ያስተዳድራሉ” (ምሳ. 8፥15-16፤ ሮሜ 13፥1-7)። የመልእክቴን መደምደሚያ፣ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ከነበሩት ኀይላትና ሥልጣናት ጋር የነበረውን ግንኝነት በምሳሌነት በመጥቀስ ይሆናል። የጌታ ምድራዊ ተልእኮ ከእነዚሁ ኀይላት ጋር አጋጭቶታል። እንዲያውም፣ የከሰሱት፣ የፈረዱበትና በመጨረሻም እንደ ወንጀለኛ የሰቀሉት የአይሁድ ሃይማኖትና የሮም መንግሥት ኀይላት በጣምራ በመሆን ነበር፤
“እናንት ግብዞች የኦሪት ሕግ መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ! ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና፤ እነዚያን ሳትተዉ እነዚህን ማድረግ በተገባችሁ ነበር” (ማቴ 23፥23)
1. ፈሪሳውያን:— የሮማን መንግሥት የሚንቁና ከእርሱም ጋር መተባበር የማይፈልጉ ነበሩ።
2. ሰዱቃውያን:— የሮማውያንን አገዛዝ ተቀብለው፣ ከፖለቲካው ኀይል ሚዛን ጋር ተሰማምቶ መኖር ይሻላል የሚሉ ሰዎች ነበሩ።
3. አሴናውያን:— ፈሪሳውያንን ሃይማኖታዊውን ሥርዐትና ቤተ መቅደሱን ያረከሱ፣ ሰዱቃውያንን ደግሞ ከሮማውያን ክፉ አገዛዝ ጋር ተባባሪዎች በመሆን፣ መንፈሳዊ ቀውስ ያመጡ ናቸው በማለት ይኰኑኗቸው ነበር። ከዚህ አስተሳሰብ የተነሣ፣ ከኅብረተሰቡ ተለይተው ለብቻቸው ብሕትውናን መንፈሳዊ መርሆ በማድረግ ከእስራኤል መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ራሳቸውን ያገለሉ ነበሩ።
4. ቀናተኞቹ/ቀናዕያን:— ፈሪሳውያንን እንደ ግብዝ፣ ሰዱቃውያንን እንደ አቋም የለሾች፣ አሴናውያንን ደግሞ ለአገር የማይገዳቸው “አክራሪ ሃይማኖተኞች” በመቊጠር፣ የሮም መንግሥት በጦር ካልሆነ በስተቀር በሰላማዊ መንገድ አይወድቅም የሚል አቋም የነበራቸው፣ “ታጋዮች” ነበሩ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአራቱም አመለካከቶች ጋር ተጋጭቷል። ከዚህ የምንማረው:—
1. ተግባር የጎደለው የፈሪሳውያን መንፈሳዊነት፣ ድኾች እንዲበደሉና ጩኸታቸውም ሰሚ እንዳያገኝ ያደርጋል።
2. በመንግሥት ላይ የሚደገፈው የሰዱቃውያን ዐይነት መንፈሳዊነት፣ ድኾች እንዲበደሉና ጩኸታቸውም ሰሚ እንዳያገኝ ብቻ ሳይሆን፣ መንፈሳዊ ተልእኮን ከመንግሥት አጀንዳ ጋር ያጋባል። በሌላ አገላላጽ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከመንግሥት የሚለየውን ድንበር ያደበዝዛል።
3. ገለልተኛው የአሴናውያን ዐይነቱ መንፈሳዊነት ደግሞ፣ “አገሬ በሰማይ ነውና በዚህ ምድር የሚሆነው ድሮም ከችግር ስለማይጸዳ አይመለከተኝም” በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ፣ ክርስቲያናዊ ተልእኮን ወደ ገዳማዊነት አስተሳሰብ ይወስዳል። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ተስፋ፣ ብርሃንና ጨው እንድትሆን ወደ ዓለም ልኳታል። በተቃራኒው፣ አሴናዊ መንፈሳዊነት ዓለምን በተስፋ ቢስ ጨለማ ውስጥ ይተዋታል።
4. የቀናተኞች/ቀናእያን የሚከተሉት አካሄድ ደግሞ፣ ፍትሕን ለማስፈን ዐመፅ ስፍራ አለው ወደሚል ድምዳሜ የሚወስድ ነው። ይህ አመለካከት ደግሞ፣ የፍትሕን ጥያቄ በዐመፅ ለመፍታት ከሚደረገው እንቅስቃሴ ጋር፣ ቤተ ክርስቲያንን ያወዳጃል። በዐመፅ መፍትሔ አይመጣም፤ ምክንያቱም ዐመፅ ዐመፅን ይወልዳል፤ ዑደቱም ከቂም፣ ከድኽነት፣ ከመከራና ከሥቃይ አዙሪት ነጻ የማይወጣ ትውልድ ማትረፍ ይሆናል!
ታዲያ ከዚህ ወዴት እንሂድ?
1. ተሐድሶ ያስፈልገናል። ቤተ ክርስቲያንን ክርስቶሳዊ አካልነትዋን አሳንሶ፣ እንደ ማንኛውም ተራ ማኅበራዊ ስብስብ እንድትሆን ከሚያስገድዳት መንገድ የሚመልሳት ተሐድሶ ያስፈልጋታል። ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ የወንጌልን ሀብት ለትውልድ የማውረሻው መንገዱ ይኸው ነውና። ስለዚህ እኛም እንደ ዳዊት:— “የሠራዊት አምላክ አቤቱ መልሰን፤ ፊትህንም አብራ፤ እኛም እንድናለን” (መዝ. 80፥19) ብለን ልንጮኽ ይገባል። በርግጥም እንደ ዕንባቆም:— “እግዚአብሔር ሆይ ዝናህን ሰምቻለሁ . . . በእኛም ዘመን አድሳቸው፤ በእኛም ዘመን እንዲታወቁ አድርግ” (ዕን. 3፥2) በማለት የእግዚአብሔርን የማዳን ኀይል የሚዘክረውን ጸሎት፥ የአገልግሎታችን ሁለንተናዊ የውስጥ ግፊት ልናደርገው ይገባል። የግል ተሐድሶ የቤተሰብ ተሐድሶን ያመጣል፤ የቤተሰብ ተሐድሶ የቤተ ክርስቲያን ተሐድሶን ያመጣል፤ የቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ የአገር ተሐድሶን ያመጣል። የጽድቅ ተጽእኖ የማምጫው መንገዱ ይኸው ነው። ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር መንግሥት ልዩ ምልክት እንድትሆን ተጠርታለች። ዓለም በታመመበት በሽታ እርሷም ከተያዘች፣ ፈውስ ልታመጣ እንዴት ትችላለች? የክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዝሙር፣ እንደ ቀደመው ሕይወቱ ሊኖር ወይም ዓለምን በቀደመው ዐይኑ ሊመለከታት አይችልም። የዘመነኛዋ ቤተ ክርስቲያን ተግዳሮት “መናገር” ሳይሆን “መኖር” ነው፤ ማለትም “ቃል” ሳይሆን “ተግባር” ነው። ለእግዚአብሔር ክብር የሚያመጣውና ዓለምም ከቶ ልትቋቋመው የማትችለው በተግባር የሚገለጠውን ፍሬአማ ሕይወት ነው።
2. ለእግዚአብሔር ክብር የሚያመጣ የአመራር ተሐድሶ። ቢያንስ 20% (20 ሚሊዮን) የወንጌል አማኞች ያላት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን፣ ተጽእኖ ማምጣት የሚያስችል የአመራር ተሓድሶ ያስፈልጋታል። የአንድ ክርስቲያን ትውልድ መንፈሳዊ ልምምድ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተደማጭነት፣ እንዲሁም የጽድቅ ተጋቦት በመሪዎቹ መንፈሳዊ ብስለት፥ የውስጥ ግለት እና የራእይ ልቀት ይወሰናል። ተመሪ የሚመስለው መሪውን ነው! በክርስቶስ ሕይወትና ሥራ የተነካና የተቀየረ መሪ፣ ለትውልድ በረከት ነው። በዓለም ዐቀፍ ሉተራን ፌዴሬሽን ጣልቃ ገብነት ከእስር ቤት ተፈተው ስደቱ ጋብ እስኪል ከአገር እንዲወጡ መንገድ ቢመቻችላችውም፣ ከመንጋው ጋር መከራን ለመቀበል በመወሰናቸው በደርግ ጭከና ሕይወታቸው በለጋነት የተቀጨው የመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን መሪ የነበሩት የቄስ ጉዲና ቱምሳ የመጨረሻ ቃል በኢትዮጵያ ክህነታዊ አደባባዮች እንደ ገና ሊስተገባ ያስፈልገዋል። ያም፣ “በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ” (2ቆሮ. 5፥15) የሚለውን ከጠቀሱ በኋላ፣ “በፍጹም አላመልጥም፤ አላደርገውም!” ያሉት የሰማዕትነት ቃል ነው። ለወንጌል እውነትና ተልእኮ መኖርና ትውልድን ማገልገል ማለት ይኸው ነው። የመልእክታችን ጒልበት የሚወሰነው፣ በተነካንበት አምላካዊ ጣት የጒልበት መጠን ነው። ያልተነካና ያልተለወጠ ምስክር ሊሆን አይችልምና! የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈቃድ በሙሉ ልብ በማገልገል ያረፈ፣ የትውልድን ጥያቄ በመመለስ ያሳረፈ አመራር ያስፈልገናል።
3. የመንግሥት የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ አፈጻ ጸም ተኣማኒነትየሚለካው “ለመልካም ነገር የሕዝብ አገልጋይ” (God’s servant for the common good of all) መሆን በመቻሉ ወይም ባለመቻሉ ነው። በእግዚአብሔርም የፍትሕ ሚዛን ይኸው “መልካም አገልጋይነት ነው”። የመንግሥትም የመልካም አስተዳደር ተጠያቂነት ከዚህ መሠረታዊ እውነት አንጻር ነው፤ “ፍትሕ የጎደለውን ሕግ ለሚያወጡ፣ ጭቆና የሞላበትን ሥርዐት ለሚደነግጉ ወዮላቸው! የድኾችን መብት ለሚገፉ፣ የተጨቆነውን ሕዝቤን ፍትሕ ለሚያዛቡ፣ መበለቶችን ለሚበዘብዙ፣ ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ለሚመዘብሩ ወዮላቸው!” (ኢሳ. 10፥1-2፤ ማቴ. 25፥34-39፤ ሉቃ. 11፥42)። ከማናቸውም አድሎአዊነት በጸዳ መልኩ፣ የሰውን ሁሉ ክቡርነትና እኩልነት መሠረቱ ያደረገ መልካም አስተዳደር ለምድራችን ፈውስ ነው። የመናገር፣ የማሰብ፣ ሀሳብን በሰላማዊ መንገድ የመግለጽና የሃይማኖት ነጻነት፣ እግዚአብሔር በመግቦቱ ለሰው ሁሉ የሰጠው ሊፋቅ የማይገባው መብት ነው። መቼም ቢሆን ፈሪሓ እግዚአብሔር ያለው፣ በጽድቅ፣ በፍትሕና በምሕረት ላይ የተመሠረተ አመራር ለብሔራዊ አንድነትም ሆነ ለጋራ ብልጽግና ወሳኝ መሆኑን ማሳስብ ያስፈልጋል። ትርጒም ያለው ውይይትም ሆነ የጋራ ዕድገት የሚመጣው በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አሠራር ሲኖር ነው። ይህም ማለት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የኀይል ሚዛኑን በጠበቀና ብሔራዊና ክልላዊ ብልጽግናን ባማከለ ራእይ መመራት መቻል ማለት ነው። በዚህ አንጻር የአገር መሪዎች የሥልጣን ሁሉ ባለቤት የሆነውን እግዚአብሔርን በመፍራት በፍትሕ፣ በጥበብና በማስተዋል እንዲያስተዳድሩ ቤተ ክርስቲያን የትውልዱ ኅሊና መሆን ይኖርባታል። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተልእኮአዊ ዐውድ ድኽነትን ከመፋለም ጋር የተቈራኘ ነው። የወንጌል መልእክቷ ለድኾችና ከዕውቀት ማነስ የተነሣ ለራሳቸው መብት መቆም ለማይቸሉ፣ ከሀገሪቱና ከዓለም ዕድገትና ብልጽግና ክልል መስመር ውጭ ላሉ ዜጎች በእርግጥ “የምሥራች” ሊሆን ይገባዋል።
4. ተልእኮአችን ብሔራዊ ዕርቅና ተሐድሶ እንዲመጣ በሚደረገው ውይይት ውስጥ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ተሳታፊነትን ይጨምራል። በእርግጥ የክርስቶስ ተልእኮ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ እንዳልነበረ ሁሉ፣ ቤተ ክርስቲያንም ሊኖራት የሚገባው የራስ ግንዛቤ ይኸው ሊሆን ይገባል። ይሁን እንጂ መልእክታችን የማይነካው የሰው የኑሮ ድንበር የለውም። የክርስቶስ፣ “የእግዚአብሔር መንግሥት” መልእክት ከሮም ጋር አጋጭቶታል። እርሱ በእግዚአብሔርና በሰው፣ በሰውና በሰው መካካል ያለውን የጥል ግድግዳ ለአንዴና ለዘላላም አፍርሷል። ልክ እንደዚሁ፣ እርሱ በእርግጥ ጌታዋ የሆነላት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ጎሣዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ጽንፈቶች ለምትታመሰው ዓለም አስታራቂና ፈውስ ናት። ከዚህ አንጻር፣ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ኀጢአት ከበዳይና ክፉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገዛዞች፣ አስተሳሰቦችና ባህሎች ጋር እንደ ድርና ማግ የተጠላላፈ መሆኑን ግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባዋል። በክፍል አንድ ለመግለጽ እንደ ሞከርሁት፣ ምድራዊው ኑሮአችን ከምድራዊ ዜግነታችን እንዲሁም የሕይወት ትግልና ተስፋ ጋር ተሰናስሏል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነው ነገር ሌሎችን በሚመለከትበት መጠንና ደረጃ እኛንም በደጉም በክፉም ይመለከታል። ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶች ባይተዋር ልንሆን አንችልም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን “የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ነው” (ራእ. 17፥15)፣ ስንል የጌትነቱና የገዥነቱ አድማስ በምድር ነገሥታት ሁሉ ላይ ነው። ቤተ ክርስቲያንንም “ወደ ምድር ሁሉ”(ማቴ. 28፥18-20) ሂጂ በማለት የላከበት ሥልጣን፣ ይኸው ወሰን የሌለው ጌትነት ነው። ግብረ ሰዶማዊ የመንግሥት ዐዋጅ፣ አድሎአዊ አስተዳደሮችና ፖሊሲዎች ከክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ጋር በመጋጨታቸው ተቃውመን፣ የንጹሓን ደም ሲፈስ፣ መሠረታዊ ሰብአዊ መብቶች ሲረገጡና ኢፍትሐዊነት ሲነግሥ ተመልከተን ጀርባ ከሰጠን ግብዝነት ነው።
5. የፍትሕ ጥያቄ ክርስቲያናዊ ምላሽ እሴታዊ መሠረቱ፣ አምላካችን ለተበደሉ፤ ለተጨቆኑና ለድኾች ጩኸት የሚራራ አምላክ መሆኑ ነው፤ “መልካም ማድረግን ተማሩ፤ ፍትሕን እሹ፣ የተገፉትን አጽናኑ፤ አባት ለሌላቸው ቁሙላቸው፤ ለመበለቶችም ተሟገቱ” (ኢሳ. 1፥17)። እውነተኛ አምልኮ ከፍትሕ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው (ያዕ. 1፥27፤ 2፥15-17፤ ሚክ 6፥8፤ 1ዮሐ. 3፥17)። ተግባር ወይም ጽድቅ የጎደለው የፈሪሳውያን መንፈሳዊነት፣ በመንግሥት ላይ የተደገፈ ሰዱቃዊነት፣ ገለልተኛው የአሴናውያን የፍትሕ እይታና ፍትሕን ከዐመፅ ጋር ያጋባው የቀናተኞች የራስ ግንዛቤ ለቤተ ክርስቲያን አዋጪ አይደሉም። የእውነተኛ ፍትሕ መንገድ እውነትና ምሕረት፤ ጽድቅና ሰላም መገናኘት ነው። ቤተ ክርስቲያን አስታራቂ ናት። ማስታረቅ ማለት ይኸው ነው። ዓለምን በሕይወት ምስክርነትና በቃል በጽድቅ መኮነን ማለት፣ ኀጢአትን ኀጢአት፣ ግፍን ደግሞ ግፍ እንዲሁም በደልን በደል ማለት መቻል ነው። በእርግጥ ክርስቶስ ጌታዋ የሆነላትና የመስቀሉን መንገድ ድልድይ ያደረገች ቤተ ክርስቲያን፣ በበዳይና በተበዳይ መካከል በመቆም የዕርቀ ሰላም መንበር መሆን ትችላለች። በአሁኑ ጊዜ የሦስቱ ታላላቅ ቤተ እምነቶች፣ ማለትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የወንጌላውያን አማኞችና የካቶሊኮች ቊጥር 62% እንደሚደርስ ይገመታል። የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ደግሞ የኦርቶዶክሳውያን ቊጥር 42–45%፣ የወንጌላውያን አማኞች ቊጥር 18–21%፣ የካቶሊኮች ቊጥር 1% ይሆናል። ይህን ስሌት ያመጣሁት ክርስቲያኖች ሰላምና ዕርቅ እንዲመጣ በሚደረገው ትግል ውስጥ፣ “ለእግዚአብሔር እንደ ተለየ ሕዝብ” ክርስቶስን ማዕከል ያደረግ ንቁ ተሳትፎ ቢያደርጉ ሊያበረክቱ የሚችሉትን ድርሻ ለመጠቆም ነው። እንደ ቃሉም በምድራችን፣ “ፍትሕ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅም እንደማይደርቅ ምንጭ ይፍሰስ” አሜን! (አሞ 5፥24)!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይጠብቅም!
ግርማ በቀለ