እየሩሳሌም የማን ናት?
በመካከለኛው ምስራቅ በምትገኘው የእየሩሳሌም ከተማ ምክንያት ዘመናትን ያስቆጠረ ጦርነትና እልቂት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ የሐገር መሪዎች ማዶ ለማዶ ሆነው በፉከራና በማስፈራራት ከሚወራወሩት ቃላትና ከሚያምዘገዝጉት ሐገር አቁዋራጭ ሚሳይሎቻቸው አልፈው በጥይት ይጠዛጠዛሉ፣ በሳንጃ ይዘነጣጠላሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ ደም አፋሳሽ ጠብ ዋናው ምክንያት ደግሞ ይህች የኢየሩሳሌም ከተማ ለእኛ ትገባናለች፣ የእኛ ቅደስት ከተማ ናት በሚሉ የሐይማኖት መሪዎች መሐከል የተነሳ ንትርክ ነው፡፡ እየሩሳሌም ለማን እንደምትገባ ለመፍረድ የእኔ ሐላፊነት ባይሆንም አንድ በትክክል መናገር የሚቻለው ከተማዋ በርግጥ የተቀደሰች መሆንዋን በሶስት ምስክር (በአይሁድ፣ በክርስቲያን፣ በእስላም) ተረጋግጦአል፡፡ የዚህ ጽሁፍ አላማ ከተማዋ ከእነዚህ ሶስት ግዙፍ የእምነት ዘርፎች የማን እንደሆነች ለማስረዳት ሳይሆን አይሁዶች፣ ክርስቲያኖችና እስላሞች ይህችን ከተማ ‹‹ትገባናለች››፣ ‹‹የእምነታችን ቅድስት ስፍራ ናት›› የሚሉበትን ምክንያት ለማካፈል ብቻ ነው፡፡
እየሩሳሌም በአይሁዶች እይታ
በብሉይ ኪዳን መጻህፍት ኢየሩሳሉም ከተጠቀሰችባቸው ስሞች መሐከል ሳሌም፣ ሞሪያ፣ እና ጽዮን የሚሉ ይገኙበታል፡፡ አይሁዶች የአብረሐም ዘር ያላቸው በመሆኑ በኢየሩሳሌም ከሚገኘው የሞሬ ተራራ ጋር ከፍተኛ ትስስር አላቸው፡፡ ይህ ስፍራ በዘፍጥረት 14፣18 ላይ አብረሐም ከመልከ-ጸዴቅ ጋር የተገናኘበት የንጉስ ሸለቆ ተብሎ የተጠራው በሞሪያ (እየሩሳሌም) እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በዘፍጥረት 22፣1-19 ደግሞ አብረሐም ይስሐቅን ለመሰዋት የወሰደበት ቦታ ስለሆነ ለአይሁዶች የተቀደሰ ስፍራቸው ነው፡፡ በሞሬ ተራራ ላይ ያለው አብረሐም ልጁን ለመሰዋት ተዘጋጅቶበታል የሚባለው አለት ‹‹የመሰረት ድንጋይ›› (Even Shetiyah) ብለው የሚጠሩት ሲሆን የአለም ሁሉ መንፈሳዊ ነገር የጀመረው እዚህ ስፍራ እንደሆነ በአጽኖት ይገልጻ፡፡ ይስሐቅ በዘፍጥረት 24፣63-67 ባለው ክፍል ርብቃን ከማግኘቱ ፊት የጸለየበት ስፍራና ያእቆብ በዘፍጥረት 28፣ 10-22 ላይ የሰማይ መስኮቶች ተከፍተው መላእክት በመሰላላ ሲወጡና ሲወርዱ ሕልምን ያየበት ስፍራ ይህ የሞሬ ምድር የተባለው እየሩሳሌም እንደሆነ ያምናሉ፡፡
የእየሩሳሌም ምድርና የሞሬ ተራራ ለአይሁድ ሕዝብ በሺህ ለሚቆጠሩ አመታት እንደ ብቸኛ የተቀደሰ ስፍራ አድርገው በመመልከት ቤተ-መቅደሳቸውን ሰርተውበት ነበር፡፡ የአይሁድ ቤተ-መቅደስ ፈርሶ በምትኩ መስኪድ በተሰራበት በአሁን ዘመን እንኩዋን አይሁዶች በቀን ሶስት ጊዜ የሚጸልዩት ፊታቸውን ወደ ኢየሩሳሌም አድርገው ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ሆኖ የሚጸልይ ደግሞ ፊቱን ወደዚህ ቤተመቅደስ አዙሮ ይጸልያል፡፡ በአይሁዶች ጸሎት ውስጥ ‹‹ኢየሩሳሌም›› የሚለው ቃል በርካታ ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን አይሁዶች የፋሲካ በዓላቸውን ሲያጠናቅቁ የሚሰነባበቱት‹‹በሚቀጥለው አመት በእየሩሳሌም እንገናኝ›› በሚል የመልካም ምኞት መግለጫ ነው ፡፡
እስራኤሎች ከግብጽ ባርነት ተላቀው ወደ ከነአን ከገቡት እስከ ነገስታት ዘመን ባለው 400 አመታት ኢየሩሳሌም የአይሁዶች ከተማ አልነበረችም፡፡በ2ሳሙኤል 5 መሰረት እየሩሳሌምን ከከነአናዊያን በመውሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ የአይሁድ ከተማ ያደረጋት ንጉስ ዳዊት ነው፡፡ ዳዊት ቤተመቅደስ ለማሰራት የሚያስፈልገውን እቃ ሁሉ አከማችቶ ልጁ ንጉስ ሰለሞን የመጀመሪያውን ቤተመቅደስ በእየሩሳሌም አሰርቶበታል፡፡ ይህ ቤተመቅደስ 410 አመት አገልግሎት ከሰጠ በሁዋላ ባቢሎናዊያን ስላፈረሱት አብዛኛዎቹ አይሁዶች ከእየሩሳሌም ለቀው ወደ ባእድ ሐገር እንዲሰደዱ ተደርገዋል፡፡ አይሁዶች በግዞት ምድር ለሐምሳ አመት ቆይተው ባቢሎኖች በፐርሽያ ሲሸነፉ አይሁዶች ደግሞ በዘሩባቤል አማካኝነት ወደ ሐገራቸው ተመልሰው ለሁተኛ ጊዜ በቀደመው ፍርስራሽ ላይ ሁለተኛውን ቤተመቅደስ ሰሩ (ነሕምያ 4-6)፡፡ ሁለተኛው ቤተመቅደስ ከክርስቶስ ልደት በሁዋላ በ70 ዓ.ም በሮማውያን ከፈረሰ በሁዋላ ግን የቤተመቅደሱ ስፍራ ለ600 አመታት ምንም ሳይሰራበት ፍርስራሽ ሆኖ ቆይቶአል፡፡ ምንም እንኩዋን አይሁዶች በአለም ዙሪያ ተበትነው አቅም ስላጡ የቤተመቅደሱ ስፍራ ለረጅም አመታት ባዶ ቢሆንም እስራኤሎች ስፍራው የተቀደሰ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ እስከዛሬም ድረስ እምነታቸውን በማጽናት አይሁዶች የሚጠብቁት መሲሐቸው ሲመጣ ሶስተኛውና የመጨረሻው ቤተመቅደስ በዚሁ ስፍራ እንደሚሰራ በተስፋ ይጠብቃሉ፡፡
እየሩሳሌም በክርስቲያኖች እይታ
እየሩሳሌም ክርስቶስ የተወለደባት፣ ያደገባት፣ ያገለገለባትና የተሰቀለባት ከተማ ስለሆነች ለክርስቲያኖች ከፍተኛ ስፍራ አላት፡፡ በሉቃስ 2፣22 ላይ ጌታ ከማርያምና ከዮሴፍ ጋር ለፋሲካ በአል የሄደው ወደዚህ በእየሩሳሌም ወደሚገኝ ቤተመቅደስ ነው፡፡ በተጨማሪም እየሱስ በእሩሳሌምና በቤተመቅደሱ ውስጥ እንዳስተማረና ብዙዎችን እንደፈወሰ ወንጌላት ያስተምራሉ፡፡ በአራቱም ወንጌላት መጨረሻ ላይ ጌታ የመጨረሻውን እራት በእየሩሳሌም እንደበላም ይመሰክራሉ፡፡
በክርስቲያኖች አመለካከት በአይሁዶችና በእሩሳሌም መሐከል ያለው ትስስር እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የመጀመሪያውን ኪዳን ከመረጣቸው ሕዝቦች ጋር ያደረገው እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ክርስቲያኖች በእየሩሳሌም የይገባኛል ክርክር ውስጥ በቀጥታ ባይገቡም በአብዛኛው አይሁዶችን ሲደግፉ ይታያሉ፡፡ ከዚህ በላይ ክርሰቲያኖች እየሩሳሌም የመሄድ፣ ቤተክርስቲያን የመስራትና የማምለክ መብት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ የቀደሙት ክርስቲያኖችም እየሩሳሌምን እንደተመረጠች ስፍራ ይመለከቱዋት እንደነበር አንዳንድ ማስረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አንዳንድ የወንጌል አማኝ አብያተ ክርስቲያኖችም በመጨረሻው ዘመን ጌታ ዳግም ሲመጣ በዚሁ ስፍራ ቤተመቅደስ እንደሚሰራና አለምን እንደሚገዛ ያስተምራሉ፡፡
እየሩሳሌም በእስላሞች እይታ
የእስልምናን እምነትን በ622 ዓ.ም የመሰረተው ነብዩ ሞሐመድ በመካ የተወለደ ሲሆን፣ የትውልድ ስፍራው የሆነችው ቦታ ለእስላሞች የተቀደሰች ከተማ ሆናለች፡፡ ከመካ በተጨማሪም መዲና ሁለተኛዋ የተቀደሰች ስፍራቸው ናት፡፡ እስላሞች ከእየሩሳሌም ጋር ያላቸው ትስስር የጀመረው ከክርስቶስ ልደት ከ700 አመት በሁዋላ ነው፡፡ ነብዩ ሞሀመድ አንድም ጊዜ እየሩሳሌም ሔዶ የማያውቅ ሲሆን እየሩሳሌም የሚል ስም በቁርአን ውስጥ አንድም ቦታ አልተጠቀሰም፡፡ ምንም እንኩዋን ሞሐመድ እየሩሳሌምን ሳይረግጥ ቢሞትም የእስልምና እምነት ተከታዮች ሞሐመድ ‹‹የለሊት ጉዞ›› በሚለት ተአምራዊ ሁኔታ እየሩሳሌምን እንደጎበኛት ይናገራሉ፡፡ ሞሐመድ ከሞተ በሁዋላ የእርሱ ተከታይ በሆነው በካሊፋ የሚመራ ጦር እየሩሳሌምን በ638 ዓ.ም በመያዝ ከመካና መዲና ቀጥላ ሶስተኛ የተቀደሰች ስፍራቸው አድርጎአታል፡፡ ይህንንም እምነታቸውን የሚገልጽ በሞሬ ተራራ ላይ አሁን ያለውን ‹‹አል-አቅሻ›› የተባለውን መስኪድ በአይሁዶች ቤተመቅደስ ፍርስራሽ ላይ ሰሩበት፡፡ የሞሬ ተራራ ላይ የሚገኘው አለት ሞሐመድ ወደ ሰማይ በመላኩ ገብረኤል ታጅቦ ያረገበት ስፍራ እንደሆነ በማመልከት የእስልምና እምነት ምልክት የሆነው ክብ እና ወርቃማ ‹‹ዱም›› ተሰርቶበታል፡፡
ከ638 እስከ 1917 ባሉት ረጅም አመታት አይሁዶች በምድር ሁሉ ስለተሰደዱ እየሩሳሌም እንደ ሶሪያ፣ ግብጽ፣ ቱርክ በመሳሰሉ የእስልምና እምነት ተከታዮች ቁጥጥር ስር ነበረች፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም የእስልምና ተከታይ መንግስታት እየሩሳሌምን ዋና ከተማቸው አላደረጉአትም ነበር፡፡

ላለፉት 3000 አመታት ከአይሁዶች ቀጥሎ እየሩሳሌምን ለጥቂት ጊዜ ዋና ከተማቸው ያደረጉአት ከ1099 እስከ 1187 ዓ.ም የላቲን መንግስት ተቀናቃኝ ሽምቅ ተዋጊዎች ብቻ ናቸው፡፡
እስራኤል እንደገና እንደ ሎአላዊ ሐገር በ1948 ዓ.ም ስትመሰረት በ1967 በተደረገው “የስድስቱ ቀን ጦርነት” አይሁዶች ከ2000 አመት በላይ በእስልምና እምነት ተከታዩች ተይዞ የነበረውን የእምነታቸው መሰረት የሆነውን አሮጌ ከተማ (Old City) በመባል የሚታወቀውን የቤተመቅደሱን አካባቢ በቁጥጥር ስር አደረጉ፡፡ አይሁዶች አካባቢውን ከተቆጣጠሩ በሁዋላ እስላሞችን ከማስወጣትና መስኪዳቸውን ከማጥፋት ይልቅ የ‹‹ዲፋክቶ›› ስምምነት ተፈራርመው ሰላማዊ ግንኙነት ጀመሩ፡፡ ስለዚህ ምንም እንኩዋን አይሁዶች ሎአላዊ ሐገር በመሆን እስራኤልንና አካባቢውን ቢቆጣጠሩም ይህንን የእምነት እምብርት የሆነውንና አሁን መስኪድ ያለበትን ስፍራ የሚቆጣጠሩት እስላሞች ናቸው፡፡
እየሩሳሌም የሰላም ምድር ሳሌም ብትባልም በምድር ላይ እንደዚህች ከተማ ከፍተኛ ጦርነትና ግጭት የተደረገበት ከተማ የለም፡፡ አይሁዶችም እስላሞችም ከአብረሐም ዘር ስለሆንን ይህ ስፍራ ለእኛ ይገባል ይላሉ፡፡ ሁለቱም እምነቶች በዚህ ስፍራ የእምነታቸውን ከፍተኛ መግለጫ የሆነውን መስኪድና ቤተመቅደስ ሰርተዋል፡፡ አይሁዶች የእግዚአብሄር የማይለወጥ ተስፋ ወራሾች እነርሱ ብቻ እንደሆኑና ይህ ስፍራም እግዚአብሔር ለአባታቸው የሰጣት እንደሆነ ብሉይ ኪዳንን ጠቅሰው ያስረዳሉ፡፡ እስላሞች ይህንን ባይክዱም አቀራረባቸው ለየት ይላል፡፡ በእስልምና እምነት እግዚአብሔር ሕጉን መጀመሪያ የሰጠው በብሉይ ኪዳን እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ክርስቶስ ከመጣና ከተወለደ በሁዋላ የሙሴ ሕግ የማያስፈልግ ጥቅም የሌለው ስለሆነ ሰው ሁሉ በ‹‹ነብዩ እየሱስ›› ሊያምን ይገባዋል ይላሉ፡፡ እየሱስ አገልግሎቱን ከጨረሰ በሁዋላ እግዚአብሔር የመጨረሻውን ነበይ ሞሐመድን ለሰው ልጆች እንደላከ ይናገራሉ፡፡ ከሞሐመድ በሁዋላ የእየሱስ ታሪክና ወንጌል እንዳረጀና በምትኩ ቁርአን ለሰው ልጆች ሁሉ እንደተሰጠ ያምናሉ፡፡
ይህንን ሁሉ ችግርና ግጭት ስንመለከት በሰው አእምሮና በፖለቲካ አመራር የሚፈታ ችግር አይደለም፡፡ እኛ በመጨረሻው ዘመን ላይ እንዳለን እናውቃለን፡፡ ክርስቶስ ሲገለጥ የምድር ፖለቲካና ንትርክ ሁሉ ያበቃና አዲስ ሰማይና ምድርን እንጠብቃለን፡፡ ስለዚህም ታላቁን ተስፋችንን “ማራናታ!” ጌታ ሆይ ና እንላለን፡፡