መጽሐፍ ቅዱስና ብልጽግና ከወንድም ምኒልክ አስፋው

በዚህ አጭር መጣጥፍ መጽሐፍ ቅዱስ ብልጽግናን በተመለከተ የሚያስተምረው ምንድን ነው? የሚለውን ለመመልከት ጥረት
እናደርጋለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ብልጽግና የሚያስተምረውን ከመመልከታችን በፊት “የብልጽግና ወንጌል” ምን እንደሚያስተምር በጥቅሉ
መዳሰስ ይኖርብናል። የብልጽግና ወንጌል አስተምህሮ በአብዛኛው የተመሠረተው በመዝ 34፥10፤ 37፥25 እና በ3ዮሐ 2 ላይ ነው፤ መዝሙረኛው “እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ግን ከመልካም ነገር ሁሉ አይጐድሉም”፤ “ጻድቅ ሲጣል ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም” ይላል። ዮሐንስ በበኩሉ “ወዳጅ ሆይ፤ ነፍስህ እንደሚከናወን በነገር ሁሉ እንዲከናወንልህና [እንድትበለጽግና] ጤና እንዲኖርህ እጸልያለሁ” ይላል። ትምህርቱን ባጭሩ “ብልጽግና የእግዚአብሔር በረከት ነው፤ ድህነት የእግዚአብሔር እርግማን ነው” በሚለው ማጠቃለል ይቻላል። ብልጽግና የበረከት እንዲሁም ድህነት የእርግማን ምልክት ከሆነ ለመባረክና ከድህነት ለመውጣት ምን እናድርግ? የትምህርቱ መሐንዲሶች በርካታ መፍትሔ አላቸው፤ መፍትሔዎቹ በሁለት ፈርጅ መመደብ ይችላሉ። አንደኛው መፍትሔ “አዎንታዊ አዋጅ” (positive con-
fession) ነው። እባረካለሁ ብለህ አውጅ፤ እበለጽጋለሁ ብለህ አውጅ፤ የችግሬ ሥር ከነ ሰንኮፉ ተነቅሎ ጦሴን ይዞ ከእኔ ይወገዳል ብለህ አውጅ፤ ዕዳዬ ይሰረዛል ጭንቀቴም ይበናል ብለህ አውጅ። ብቻ ከአፍህ አሉታዊ ሳይሆን አዎንታዊ አዋጅ ይውጣ። ዕድልህ የተመሠረተው ከአፍህ በሚወጣው አዎንታዊ አዋጅ ላይ ነው። ሁለተኛው “የመስጠት ሕግ” (the law of giving/tithing) ነው። አንዳንዶች ይህን
አራዝመው “ከመዝራት ሕግ” ጋር ያዛምዱታል። ገንዘብ እንደ ዘር ነው፤ እናም ገንዘብ የሚዘሩ ገንዘብ ያጭዳሉ (“seed money”)። የሚሰጡ ያለ ምንም ጥርጥር ይሰጣቸዋል፤ የሚበትኑ ይሰበስባሉ። ባጭሩ የድህነት እርግማን በመስጠትና በመዝራት ሕግ ይቀለበሳል።
መቼም ከሀብትና ከብልጽግና ጋር ምንም ጠብ የለኝም። ብልጽግና ወይም ገንዘብ በራሱ እኩይ አይደለም፤ ሀብት ወይም ንዋይ በራሱ ክፉ
አይደለም። ይሁንና “ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር” እንደ ሆነ፣ ገንዘብ የሰዎችን ሁለንተና ለመቈጣጠርና ሰዎችን ከእግዚአብሔር መንገድ ለመንጠቅ ብርቱ ጉልበት እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል (1ጢሞ 6፥10፤ ሉቃ 16፥13፤ ማር 10፥17-31)። ገንዘብን ከምንም በላይ መውደድ ከዐሠርቱ ትእዛዛት መካከል የመጀመሪያውን ትእዛዝ ይተላለፋል (ዘጸ 20፥1-2)። ጳውሎስ በመልእክቱ
ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎችን በብርቱ ገሥጿል። ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች በጥፋት ማለትም በሚጎዳ ምኞትና በፈተና ወጥመድ ይወድቃሉ። እንዲያውም አንዳንዶች ባለ ጠግነትን ሲመኙ “ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወግተዋል” (1ጢሞ 6፥11) ይላል።
ባለጠጋ ለመሆን መመኘትና መጓጓት “ኑሮዬ ይበቃኛል” (1ጢሞ 6፥6) የሚለውን አዲስ ኪዳናዊ እሴት ከመጻረሩም በላይ በሁለቱ መካከል
መሠረታዊ ልዩነት እንዳለ ይገልጻል፤ የክርስቶስ ወገን የሆኑ ሁሉ የትኛውን እሴት መከተል እንዳለባቸው መምረጥ ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ እግዚአብሔርን መምሰል “ኑሮዬ ይበቃኛል” ከሚለው ጋር ሲያነጻጽር ባለጠጋ ለመሆን መፈለግን “ራስን በብዙ ሥቃይ ከመውጋት” ጋር አነጻጽሮታል። ባለጠጋ ለመሆን መፈለግ ራስን ለፈተና ወጥመድ ምቹ አድርጎ ማቅረብ ነው። “ኑሮዬ ይበቃኛል” ማለት “እጅግ ማትረፊያ
ነው”። መላው አዲስ ኪዳን ባለን ነገር ረክተን እንድንኖር ያስተምራል። አዲስ ኪዳን ትልቅ ትርፍ ወይም እሴት ነው የሚለው ባለን ነገር ረክቶ መኖርን ነው። ይህንን ነው ጳውሎስ “እውነተኛ መንፈሳዊነት” ወይም “እግዚአብሔርን መምሰል” የሚለው። የዚህ ዓለም ሰዎች የሚራቡትን መራብ ወይምየ ዚህ ዓለም ሰዎች ለሚጋደሉለት ነገር መጋደልና ለሚሰባበሩለት ነገር መሰባበር ክርስቶሳዊም መንፈሳዊም አይደለም። ጳውሎስ “የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና” (ፊል 4፥11) ይላል።