የሻለቃ ማሞ ጤናዬ (ጋሽ ማሞ ) አጭር የህይወት ታሪክ:-
ሻለቃ ማሞ ጤናዬ ከአባታቸው ከመምሬ ጤናየ አውግቸውና ከወይዘሮ ዘነበች ናደው በሰሜን ሸዋ ጅሩ እነዋሪ ወረዳ እ.ኤ.አ ኦክቶበር 9፣ 1937 ተወለዱ። እድሜያቸው ለጋብቻ ሲደርስ ጋብቻን በመመስረት የ10 ልጆች አባትና የ6 ልጆች አያት ነበሩ።
ሻለቃ ማሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በሁዋላ በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር በሆለታ የጦር መኮንኖች ትምህርት ቤት ተምረው በሰራዊቱ ውስጥ በመኮንንነትና በሁዋላም የጤና ባለሞያ በመሆን ሰራዊቱን አገልግለዋል። እንዲሁም ለተጨማሪ ስልጠና መንግስት በከፈተላቸው ዕድል መሰረት ሂዩስተን ቴክሳስ በሚገኘው US ARMY Medical Department Center and School ስልጠናቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
ሻለቃ እ.ኤ.አ 1977 በነበረው የኢትዮጵያና የሶማሌያ ጦርነት ድሬዳዋ አየር ማረፍያ የጥበቃና መከላከያ አዛዥ ሆነው በሚሰሩበት ጊዜ በግራ እጃቸውና እግራቸው ላይ በጥይት ተመትተው በአገር ውስጥ እንዲሁም በጀርመን ሃገር ህክምና ቢደረግላቸውም የደረሰባቸው ጉዳት ስራቸውን እንዲቀጥሉ ስላላስቻላቸው በራሳቸው ጥያቄና በጦርሃይሎች ሆስፒታል የሃኪሞች ቦርድ ማረጋገጫ መሰረት በሻለቅነት ማዕረግ እንዳሉ ሰራዊቱን በጡረታ ተሰናብተዋል። ሻለቃ ያካበቱትን የህክምና ሞያ በመጠቀም በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በጎሬ፣ በኢሉባቡር፣ በወልቂጤና በሰበታ የፋርማሲ ባለሙያ በመሆን ቤተሰባቸውን ይረዱ ነበር።
ሻለቃ ማሞ እ.ኤ.አ በ1988 ጌታ ኢየሱስን እንደግል አዳኛቸው ተቀብለዋል። በእምነታቸውም ከጠነከሩ በሁዋላ በልደታና በሰበታ መካነ ኢየሱስ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን በተለያዩ አገልግሎት ዘርፎች እንዲሁም በሽማግሌነት አገልግለዋል። ለሁለተኛ ጊዜ ለኑሮ ወደ ወደ አሜሪካ ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ደግሞ በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን አባል በመሆን በሰንበት ትምህርት፣ በጸሎት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና በአያቶች ህብረት ተሳታፊ ነበሩ። በተለይም ለሃያ አራት ሰዓት ያለማቋረጥ በሚካሄደው የቤርያ ቴሌኮንፍረንስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና ትምህርቶች ላይ በሚያደርጉት ተሳትፎና ምክራቸው በብዙዎች ዘንድ የተወደዱ ነበሩ። ሻለቃ ማሞ ጌታንና መንፈሳዊ ነገርን በጣም የሚወዱና አውርተውም የማይጠግቡ ነበሩ።
ጋሽ ማሞ በኬንተኪ ከተማ ለጥቂት ዓመታት በስራ ቆይተው በዐይናቸው ህመም ምክንያት ስራቸውን ማቁዋረጥ ተገደዋል። አባታችን ከዐይናቸው ህመም ተጨማሪ የአስም በሽታ ነበረባቸው። ሻለቃ ማሞ በተወለዱ በ80 ዓመታቸው ሴፕቴምበር 13፣ 2017 ከዚህ ዓለም በሞ ት ተለይተው ወደ ፈጣሪያቸው ተሰብሰበዋል።
የቤርያ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የወንጌል አገልግሎት ቤተሰባቸውን እግዚአብሔር ያጽናችሁ እንላለን።
አንድ ድምጽ ጠፋብኝ፣ ሃሎ ጋሽ ማሞ ነኝ፣
አንድ ሃሳብ ነበረኝ ጥያቄ የሆነብኝ
ላልፈው ስለማልችል መናገር አለብኝ!
አንዴ ፍቀድልኝ ጊዜህን አልወስድም
ለእኔ ብቻ ሳይሆን ይጠቅማል ለሁሉም
ብሎ የሚጀምር ቤርያ ላየን ላይ
በጥናት ፕሮግራም ዘወትር የማይለይ
ትሁት ቅን አሳቢ ጽድቅን የተራበ
ሚጠይቅ ሚያካፍል ቃል እያነበበ
ጠፍቶብን ላየን ላይ ድምጹን ከሰማነው
ለካስ ወደ ጌታ በሰላም ሄዶ ነው።
የዘላለም ሕይወት ሰላምና ደስታ
ፍጹም እረፍት ሃሴት ካለበት እርካታ
ሄዱዋል በደስታ ፈልጎ መኖርን
ተስፋውን ለማየት የሚወደው ጌታን
አንተም ታውቀዋለህ….. ወዴት እንደምትሄድ …እኛም እናውቃለን ወዴት እንደምትሄድ
ጋሽ ማሞ ደህና ሁን፣ …ይሁን እንላለን እረፍት በጌታ ዘንድ
…. እጅጉን ይበልጣል እረፍት በጌታ ዘንድ።
ግጥም ከቅዳሜና ማክሰኞ የቤርያ የስነ ጽሁፍ ክፍል