2ተኛ ጢሞ 2 : 11_13 11 ቃሉ የታመነ ነው እንዲህ የሚለው። ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፤ 12 ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው፥ እርሱ ደግሞ ይክደናል፤ 13 ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።

ትዕግስት ከተንበረከከችበት እየተነሳች፣ ይህን ቃል ዝም ብዬ አላነበብኩትም ለአንተም  ይመስለኛል በማለት ፌልድ ለስራ ለመውጣት እየተዘጋጀ ያለውን ባለቤቷን ዐይን ዐይኑን እያየች ደጋግማ ታነብለት ጀመር። ቶሚ መልካም ቁመና እንደ አለህ፣ ቆንጆ እንደሆንክም እንኳን እኔ ሚስትህ ያዩህ ሁሉ ለአንተ ያላቸው እይታ ይመሰክራል። አንዳንድ ሴቶችማ ማግባትህን እያወቁ ወይም እየረሱ እላይህ ላይ ሊሰፍሩ እኮ ትንሽ ነው የሚቀራቸው። ታድያ ይህን ሳይ እኔ ለነሱ እያፈርኩ እሳቀቃለሁ። ቶምዬ አንተን በመጠርጠር አይደለም እንደው ከሰልፍ ብዛት ባሌ ታማኝነቱን ያፈርስ ይሆን እያልኩ እሰጋለሁ ብላው ወደ መሬት እያየች ፍርሃትና ሃዘን በተቀላቀለበት ተመስጦ ፍዝዝ ብላ ትመለከት ጀመር። ቀና ብላም የአንተ ታማኝነት እኮ ለሕይወታችን ወሳኝነት አለው  መጀመርያ ለጌታ ታማኝ ከዚያም ለትዳርህ፣ ለቤተክርስትያን እንዲሁም ለሚያውቁህ ሁሉ ታማኝ መሆን እንደሚያስፈልግ የሚገባህ ይመስለኛል   ግን ቶምዬ ይህን ስጋቴን የምነግርህ ለእኔ ያለህን ፍቅር ለቅንጣት ያህል ተጠራጥሬ ሳይሆን አንተ የምትቀርባቸውን ሴቶችና የስራ ባልደረባዎችህን ሁኔታ ስመለከት እያሳሰበኝ ነው። አብሬህ እያለሁ እኮ አንዳንዶቹ ዐይን አውጥተው ይጠቅሱሃል    ሌሎቹም ሲዳሩህ በጣም ያስፈራል። ይህ ሰው ከፈተና ብዛት ይወድቅ ይሆን እንዴ እያልኩ እፈራለሁ። እየውልህ ቶምዬ በዚህ ዘመን አለመታመን መዘዙ በጣም የከፋ ነው። በአንድ ቀን ስሜታዊነት ትዳር መፍረስ ብቻ ሳይሆን ሕይወትም ይጠፋል። ልጆችም ያላሳዳጊ ይበተናሉ። እዚሁ በእኛ መስርያ ቤታችን ኢንጂነር አስናቀ የደረሰበትን ታውቃለህ   ሶስት ህጻናት ልጆቹን ትቶ ሞተ   ሚስቱ ደግሞ  ያው እንደምታውቀው በዓመቱ ሞተች። ይህ HIV የተባለ በሽታ እንደሆነ ሁሉ ሰው ያውቃል።  በፍርሃት ዐይን ዐይኑን እያየች ግራ በመጋባት ተሰናብቷት ወደ መስክ ስራ ሊሄድ የተዘጋጀውን ቶማስን መሰናበት የሞት ያህል አስፈራት። ቶማስ ሞት ይዞ ሲመጣ ታሰባትና በፍርሃት ዞር ብላ በቀስታ በኢየሱስ ስም አለች።

ቶሚ ሊያረጋጋት ትከሻዋን አቅፎ ቲጂ እረ እንደዚህ አትሁኚ   እንደዚህ ከሰጋሽ ለምን አብረሺኝ ፊልድ አንወጣም? ሲል ቲጂ ልጆቻችንስ? እንዴት ይሆናል ይሄማ አይሆንም   እኔ እኮ አምንሃለሁ ግ ግ ግ ን  ሰው ደካማ ነው  ብርቱ ነኝ ብለህ ከመጠንቀቅ እንዳትዘናጋ ለማሳሰብ ነው። ”ማስተዋል ይጠብቅሃል ጥንቃቄም ይጋርድሃል“ አይደል የሚለው መጽሐፉ ስትለው እሺ ጸልዪልኝ ብሎ  ሻንጣውን ይዞ ለደቂቃዎች ተቃቅፈው ሲያበቁ ቶሚ መኪናውን አስነስቶ  በፍጥነት ከዐይኗ ተሰወረ። ቲጂ ከቆመችበት ሳትንቀሳቀስ መጸለይ ጀመረች   ጌታ ሆይ አንተ ጠብቅልኝ፣ ወደ ፈተና አታስገባው፣  ብላ ለጌታ ሰጥታው ወደ ቤትዋ ገባች።

ቀናቶች ይሄዱ ጀመር   ቶማስ ፌልድ ከወጣ ዛሬ አራት ቀን ሆኖታል። አብረው አንድ መስርያ ቤት ስለሚሰሩ የፊልድ ውሎውን አልፎ  አልፎ  ከሌሎች የስራ ባልደረባዎቿ ትሰማለች።

ቶማስና ቲጂ በትዳር አስራ ሁለት ዓመት ሆኗቸዋል። ገና በዩኒቨርሲቲው የኢንጂነሪንግ ተማሪ እያሉ በፌሎውሺፕ ውስጥ ሲያገለግሉ ነበር ተቀራርበው በዓመቱ ለፍቅረኝነት የበቁት። ሆኖም ይህን የእጮኝነት ግንኝነታቸውን ማንም አያውቀውም ነበር ። ወንድምና እህት እንጂ ቀበጥ ያለ ሌሎችን ሊያሰናክል የሚችል ከእጮኝነት ያለፈ መቀራረብ በመሃከላቸው አልነበረም። ለቶማስ ትልቅ ማስጠንቀቅያ ከቲጂ ተሰጥቶት ነበር። ከጋብቻ በፊት አንዳች ነገር ብትሞክር ያበቃልናል የሚል ከባድ ማስጠንቀቅያ ነበር ። ቶማስም እንኳን ሊሞክር ቀርቶ አስቦትም አያውቅም ነበር። ቶማስ በቃል ሲያገለግል ቲጂ ደግሞ በዝማሬና አምልኮ መሪነት አገልጋይ ነበረች። ለአብዛኛው ተማሪ ወንድምና እህት ነበር የሚመስሉት። እስኪጋቡ ድረስ ቶማስ አንድ ቀን እንኳን ቲጂን ስሟት አያውቅም ነበር። ለብዙዎች ከጋብቻ በፊት ሊኖር ስለሚገባው የቅድስና ሕይወት እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ነበሩ። የሰርጋቸው እለት ቶማስ ተነስቶ  “ ዛሬ የእኔና የቲጂ እህትና ወንድምነት የሚያበቃበት እለት ነው” በማለት ያደረገው ንግግር የሚያውቋቸውን የዩኒቨርሲቲ ታዳሚዎችን ሁሉ ነበር ያሳቀው። ታውቃላችሁ በማለት ቶሚ ቀጠል አድርጎ  “እንደምወዳት ስነግራት እንደምትወደኝ ከነገረቺኝ በሁዋላ ተሳስተህ እንኳን ልትስመኝ ብትሞክር የእኔና የአንተ ነገር ያበቃል ብላ ስትለኝ ይገርማችኋል እጥፍ ወደድኳት   ታማኝ ሆኜላትም በቅድስና እስክንጋባ ድረስ ከተመረቅን በሁዋላ ለአራት አመት ለመቆየት ቻልኩ“ የቲጂ የቅድስና ሕይወት የእኔንም ሕይወት በበጎ ተጽዕኖ ለውጦታል። ስለ ቲጂ እግዚአብሔር ትልቅ በረከት አድርጎ  ስለሰጠኝ አመሰግናለሁ አለ። SHE IS A WOMAN OF GOD ብሎ በእንግሊዘኛ ሲያክልበት ”እውነት ነው“ በማለት የሚያውቋት ታዳሚዎች ሁሉ ሰርጉን በጭብጨባና በእልልታ አቀለጡት። ከሰርጋቸው በኋላ ቲጂን ከቶሚ ጋር ተያይዛ ስትወጣና ስትገባ የሚያዩዋት ብዙ ሴቶች በነገረኛ አይን ሳይገርፏት አያልፉም። ቲጂም ይገባታል። አንዳንዶቹም ሴቶች ይህን መሳይ ሸበላ በምን ይዛው ይሆን ደግሞ ከየት አገኝቺው እንደሚሉ ይገባታል። እሷ ጠይም፣ የደስ ደስ ያላት ጎራዳና አጭር የሴት ወይዘሮ ስትሆን እሱ ደግሞ ረጅምና ቀይ ሰልካካ ነው። በዓለም የመልክ መለክያ ሴቶች ዓይናቸውን የሚጥሉበት አይነት ነው። ታድያ ለሚያውቋት ቲጂም ልዩ የሆነች የጌታ ውብ ነች።

በአምስተኛው ቀን ቶሚ ያለመደወሉ አሳስቧት ደወለችለት። ለምን አልደወልክልኝም በማለት ቲጂ ወቀሳውን አወረደችበት ። ቶሚም እረ ስልክ አይሰራም ነበር ኔትወርኩ አልነበረም አሁን ልደውልልሽ ስል ነው የደወልሺው በማለት ሊያረጋጋት ሞከረ ። ስለልጆችና ስለስራ ካወሩ በሁዋላ  የመስርያ ቤትዋ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ወደ ቢሮው ጠርቶ እድገት ልንሰጥሽ ነው እንዳላትና እርሷም እስቲ ላስብበት ብላ እንደወጣች ነገረችው።  እሱም ምን ማሰብ ያስፈልጋል ቲጂዬ ይሄ እኮ ጥሩ ነገር ነው ሲል መለስ አድርጋ አንተ ከእኔ የተሻለ ችሎታ እያለህ ለእኔ የተሰጠበት አልገባኝም። አንተ የቡድኑ መሪ ሆነህ የምትሰራው እያለህ እኔን መሾም ማሰባቸው አይገባኝም። ይህን ለመረዳት ጾምና ጸሎት ያስፈልገዋል ብላው  ከብዙ ሌላ የቤት ጨዋታዎች በሁዋላ በፍቅር ተሰነባብተው ስልካቸውን ዘጉ።

ትዕግስት የመስርያ ቤትዋ  ቢዝነስ ሚቲንግ በሂልተን ሆቴል በ12 ሰዓት ስለሚደረግ እንድትገኚ የሚል ጥሪ ደርሷት ቀደም ብላ በሆቴሉ ተገኝታ የእንግዳ ማረፍያ ሎቢ ውስጥ ተቀምጣለች። እሷ ብቻ መገኘቷ ግር ገብቷት አስተናጋጆቹን ብትጠይቅም ምንም አይነት የቢዝነስ ስብሰባ እንደሌለ ነግረዋት ግራ ተጋብታ ቁጭ ብላ ሳለ የመስርያ ቤቷ ማነጀር አቶ አብርሃም ከተፍ አለ። እንዲህ ነው ቀጠሮ ማክበር ብሎ በፈገግታ ከጨበጣት በሁዋላ ነይ አረፍ ብለን እንጠብቃቸው ብሎ ይዟት ወደ ምግብ አዳራሹ ገባ። ምግብ ለራሱ አዞ  ምን ይምጣልሽ? በማለት ለቲጂ ለማዘዝ ሲሞክር አስቆመችው። የተነገረኝ የቢዝነስ ሚቲንግ ተብሎ ነው፣ የታሉ ሰዎቹ፣ ከስራ ሰዓት ውጪ የተጠራሁበት ምክንያትም አልገባኝም ብላ ለመሄድ ተነሳች። አቶ አብርሃም ስብሰባው ስለተሰረዘ አብራው እንድትቆይ ልመናውን ቀጠለ። “ልብ በዪ ለዚህ ሃላፊነት እድገት ልሰጥሽ እንደነገርኩሽ አትርሺ” ተጠየቅሁ እንጂ ፈቃደኝነቴን አልገለጽኩም   ደግሞ ለዚህ ስራ ብቃት ያለው ከእኔ የተሻለ ሰው ስለአለ እድገቱን ለመቀበል ፈቃደኛ አይደለሁም አለች።

የድንጋጤ ሳቅ እየሳቀ “ ሰው እድገት እንዴት እድገት ይጠላል?   በጣም ትገርሚያለሽ” ትግስትዬ ብሎ  ሲል ደህና አምሽ ብላው ፊቷን አዙራ በፍጥነት ከምግብ አዳራሹ ወጥታ ሄደች። እቤት ስትደርስ ንዴቷ አልበረደላትም ነበር። ሌሊቱን ሁሉ በአልጋዋ ዳር ተንበርክካ ስትጸልይና ጌታ በደሙ እንዲሸፍናት እንዲጠብቃትም በጸሎት ስትማጸን ነግቶ ወደ ስራዋ ሄደች።

ረፋዱ ላይ አቶ  አብርሃም ቢሮ ይፈልጉሻል ተብላ ተጠራች። ስትገባ “ ደህና አደርሽ በማለት ሰላም ብሎ ትናንት በአደረገችውና ባሳየችው ሁኔታ ወቀሳ ማሰማት ጀመረ።  አለቃሽ እኮ ነኝ በማለትም በቁጣና እድገት በሚል ድለላ ለማስፈራራትና ለማግባባት ይሞክር ጀመር። ቲጂም ለዚህ ስራ ብቃት ያለው ከእኔ የተሻለ ሰው ቶማስ ባለቤቴ ነው እርሱን መሾም ትችላለህ ስትለው የአቶ አብርሃም ቁጣ እየጋለ መጣ። ስራ ሲባል እኮ ስራ ብቻ አይደለም ስራችን የተሳካ እንዲሆን ከመንግስት ባለስልጣኖች ጋር መሻረክና ጉቦ መስጠት እና እየበሉ መብላት ያስፈልጋል። ባለቤትሽ ደግሞ ይህን አያውቅበትም። አንቺን የመረጥነው ሴት ስለሆንሽና ለዚህ ስራ ተባባሪ ትሆኚያለሽ ብዬ በመገመት ነው። ለአንቺም ድርሻሽ ከደሞዝሽ ተጨማሪ ይታሰብልሻል። ጥሩ ጥቅም የሚገኝበት ነው በእግርና በአውቶቢስ ከመጋፋት ድናችሁ ጥሩ መኪናና ቤት ገዝቶ ለመኖር የሚያስችልሽ ነው። አየሽ ዘመኑ የፈጠረው ሞደርን ቢዝነስ ይሄ ነው ። አአይ እኔ ኤክስፐርት ሆኜ እቀጥላለሁ ካልሽ ደግሞ  መንገዱን ጨርቅ ያድርግልሽ   ገብቶሻል? ሲል ቲጂ “ አዎን ገብቶኛል ኤክስፐርት ሆኜ  እቀጥላለሁ ይህን ስራ ግን መቀበል አልችልም።  ውሳኔዬ ይሄ ነው ብላ ከቢሮው ውልቅ ብላ ሄደች፤  ከትከሻዋ ላይ ትልቅ ሸክም የቀለላት መሰሎ ተሰማት።

ቲጂ ቢሮዋ ገብታ አጎንብሳ አጭር ጸሎት አድርጋ አመሰገነች። እፎ  ይይ ይ    ለካስ ፈተና መልኩ ብዙ ነው። እኔ ባለቤቴን ተጠንቀቅ ተጠበቅ እያልኩ ስሰጋ ለካስ ሰይጣን ሌላ መረብ ለእኔ አዘጋጅቷል። በኪራይ ቤት ከቦታ ቦታ እንደምንከራተት በትራንስፖርት ችግር   እንደምንሰቃይ ያውቃል    ጌታን ከአርባ ቀን ጾም በሁዋላ የፈተነው ይሄ ክፉ እኛን ደግሞ በጉቦና በመልካም ኑሮ ጉጉት ሊፈትነን መጣ። ይህንን እያሰላሰለች ሳለ  ስልክ ተደውሎላት ስታነሳ ቶማስ በመሆኑ ገረማት። ሰላምታቸውን ገና ሳይጨርሱ ሱርፕራይዝ  ላደርግሽ ነው የደወልኩት  ”ባለፈው የተወዳደርኩበት መስርያ ቤት ሊቀጥሩኝ ወስነው ስራውን እንድጀምር ጠሩኝ እኮ የሚገርምሽ ስራውን የምቀበለው ባለቤቴንም ከቀጠራችሁ ብቻ ነው ስላቸው በደስታ ለአንቺም የተሻለ ቦታ አገኙልሽ። ለአንቺም ለእኔም የተሻለ ቦታና የተሻለ እጥፍ ደሞዝ እንደሚከፍሉን ተስማምተናል፣ በተጨማሪ መስርያ ቤቱ መኖርያና መኪና ይሰጠናል። በዚያ ላይ የድርጅቱ ባለቤት ክርስትያን ስለሆነ ድርጅቱ ፌሎውሺፕ ማድረግያ አዳራሽና የጸሎት ቤት አለው።  ብቻ ምን ልበልሽ   እንደምትወጂው አልጠራጠርም ሲል ቲጂ “ አይ ጌታ ግሩምና ድንቅ ነህ እኮ! አለች በመገረም እጇን በአፏ ላይ አድርጋ” የቢሮዋ በር በመንኳኳቱ በኋላ እደውልልሃለሁ ብላ ስልኩን ዘጋች። አቶ አብርሃም ነበር። በእጁ አንድ ወረቀት ይዟል። “ አዝናለሁ አንቺ እና ባለቤትሽ እዚህ መስርያ ቤት አታስፈልጉንምና ላሰናብታችሁ ወስኛለሁ።   ለአገልግሎታችሁ ጊዚ ካሳና የሚገባችሁን የመሰናበቻ ጥቅም በሙሉ እንከፍላችኋለን። መልካምና ታታሪ ሰራተኛ መሆናችሁን የሚገልጽ ደብዳቤም እንጽፍላችኋለን ብሎ የማሰናበቻ ደብዳቢዋን በእጇ ሰጣት። እናመሰግናለን በውሳኔህ ደስ ይለናል ብላ ቲጂ ፈገግ ስትል አቶ አብርሃም ደነገጠ።  የጠበቀው ለቅሶ፣ ልመናና  መለማመጥ ነበር። አሁን የሚያየውንና  የገጠመውን የተረጋጋ ምላሽ ለመቀበል አልቻለም።  ” ምን አይነት ጉድ ነሽ?  ሲሾሙሽ እንቢ! ሲያባርሩሽ እንቢ! ለመሆኑ ጤነኛ ነሽ?እንደዚህ የተማመንሺው ምንድነው ልኖርበት የምችለው ሀብት አለኝ እንኳን እንዳትዪ በአውቶቢስ ስትጋፊ ነው የምናይሽ::  ምንድነው እንደእዚህ የተማመንሽበት ነገር?

ጌታ ነዋ! ጌታ እኮ መኖርያችን ነው፣ ሁሉን የሚቆጣጠር፣ የማይቀደም፣ ገባህ በሰዓቱ የሚደርስ የዘላለም አምላክ አለን።  ይልቅስ አንተም ንስሃ ገብተህ ይህን ጌታ ተቀበል፣ አለዝያ አንተም ይህ የምትተማመንበትና የሰበሰብከው ሃብትህ ይጠፋል ከንቱ ሆነህም ትቀራለህ ብላው እቃዋን ሰብስባ ከቢሮው ተሰናብታ ወጥታ ሄደች።