ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ውጪ አገር የሚሄድ ጓደኛውን ለመሸኘት ከተሰበሰቡት መካከል የሽኝት ፕሮግራሙን ማጠቃለያ ጸሎት የሚጸልየው ሰው እንዲህ ብሎ ጸልዮአል አሉ፡፡

“ጌታ ሆይ ይህ ወንድማችን በሚሄድበት አገር ቢዚ ከሚባል ጋኔን እንድትጠብቀው እንለምንሃለሁ፡፡” “ቢዚ” የሚባል ጋኔን መኖር አለመኖሩን መመራመራችንን ትተን ባተሌነት “ቢዚነት” የውጪ አገር አበሳ መሆኑ ቀርቶ ውስጥ አገርም የሚያስጨንቀን ጉዳይ እንደ ሆነ እንቀበል፡፡

በቀጠሮ ብዛት፣ በእንቅስቃሴ ብዛት፣ በጉዳይ ብዛት፣ በሥራ ብዛት፣ በሥራ ውጣ ውረድ፣ በማኅበራዊ ግንኙነት ብዛት፣ በሽቅብ ቁልቁል ብዛት፣ የአካላችን አውታር እስኪነዝሩ ተወጣጥረናል፤ ነፍሳችን ብን ትን እስክትል እንማስናለን፡፡ ትንፋሽ አጥሮን ስናለከልክ የሚያየን የሌላ ዓለም ፍጡር ቢኖር “ምን ሥራሥር በጥብጠው ቢጠጡ ነው እንዲህ የሚያዛብታቸው፣ የሚያሽከረክራቸው” ብሎ በጠየቀ፡፡ ለመሆኑ ምን እንዲህ ያባትለናል?

የየዕለቱ ውጣ ውረድ ነዋ! የጉረሮ መድፈን ጥሪ፣ የማኅበረ ሰብ ቦታችንን የማስጠበቅ ጥሪ፣ የነገ ምን ይሆናል ጭንቀት፣ ሌሎችም ይህን የመሳሰሉ ሁሉ፡፡ የሰው ልጅ የሚሠራውንና የሚውልበትን ሁነኛ ጉዳይ አግኝቶ በሥራ መጠመዱ በረከት እንጂ ርግማን አይደለም፡፡ ጊዜ እንደ ጅረት በሚንፎለፎልበት ልማዱ ቢነጉድ የሥራ ቦይ እየቀደዱ ጥቅም ላይ የሚያውሉት የታደሉ ናቸው “ዘመኑን ዋጁ” በሚለው ምክር አብነት፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ በሥራው ከሚገኘው ጥቃሞት በላይ ስብእናቸው ይለማል፣ ርካታና ደስታም ያገኛሉ፡፡

አሁን ያነሣነው “ጋኔኑ ቢዚነት” ግን ከሚያለማው የሚያጠፋው የበለጠ፣ ከሚያረካው የሚያቅበዘብዘው የበዛ፣ ደስታችንን ቦጥቡጦ የሚበላ መልቲ ነው፡፡

ሮጠን ሮጠን ልባችን ሊፈነዳ ሲል ስንቆም የትም እንዳልደረስን ስንረዳ፣ ከበሬታ ፍለጋ ብዙ የአንቱታ ካባ ደርበን ድንገት ካባው የወደቀ ቀን የነፍሳችን ክሳት ሲጋለጥ የዚህ ዐይነት ቢዚነት ፍሬ ይታወቅ ይሆናል፡፡

መድኃኒታችን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ “በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ ወደዚህ ምድር ስለመጣ ልክ እንደ እኛ በቀን ውስጥ 24 ሰዓት ብቻ ነበረው፡፡ ያደረገውን ሁሉ ያደረገው በዚሁ በባለ 24 ሰዓት ቀን ነበር፡፡ የምድር እድሜው ጥቂት ነበረ፤ የይፋ አገልግሎቱ ደግሞ ከሦስት ዓመታት እጅግም ያልዘለለ አጭር ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ወደ አባቱ መሄዳው ጊዜ ሲደርስ የጸለየው ጸሎት የተዋከበ፣ የተጨነቀ አልነበረም፤ “ምነው አንድ ዐሥር ዓመት ብትጨምርልኝና የጀመርሁትን በጨረስሁ” የሚል የጊዜ ልመና አልነበረበትም፡፡ “የሰጠኸኝን ሥራ በምድርላይ ፈጽሜ አከበርሁህ” የሚል ደልዳላ ዘገባ ነበር፡፡

እንዴት እንደዚህ ስክን ያለ ሕይወትና አገልግሎት አገኘ? እጅግ ብዙ የእርሱን ርዳታ የሚሹ ፍጡራን ባሉበት ዓለም ውስጥ በቀኝና በግራ ሊያዋክቡት የሚችሉ አስባታሊ ተግባራት በነበሩበት ሁኔታ እንደምን ርጋታ አገኘ? መጽሐፉ ላይ እንደ ተጠቆምን ከሆነ መልሱ ውስብስብ አይደለም፡፡ ጌታችን ዋናውን ጉዳይ ከአስቸኳዩ የለየ፣ የሕይወት ጥሪውን አሳምሮ ያወቀ፣ ቆፍጣና የዓላማ ሰው ስለነበረ ነው፡፡ “የሰጠኸኝን ሥራ” አለ እንጂ በሜዳ ያለውን ተግባር ሁሉ አላለም፤ ወይም ዘመድ ወዳጅ የጠየቀኝን ኀላፊነት ሁሉ ወይም የተገኘውን ሥራ ሁሉ ፈጸምሁ አላለም፡፡ የአባቱ ፈቃድ የሕይወት ጥሪው ነበረና ያንኑ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ፈጸመው፡፡ በጸሎቱ ዘገባ በዝርዝር እንዳሰፈረው እያንዳንዱን ቅንጣት ተግባር ከነውጤቱ እንደተከናወነ ርግጠኛ ነበር፡፡ በምድር አገልግሎቱ የነካቸው ሰዎች ሁሉ ሕይወታቸው በጥልቅ ተነክቷል፤ የይድረስ ይድረስ በሽታ ሳይጠናወተው የሚሠራውን ሁሉ ወደ ተገቢው ፍጻሜ አደረሰ፡፡ በዓላማ ጽናት፣ በርግጠኛ ርምጃ፣ በታላቅ ማስተዋል ተራመደ፡፡ ስለዚህ ሞቱ የጸጸት አልነበረም የድልና የስኬት እንጂ፡፡ ሕይወቱ አልተጨናገፈም፤ ውጥኑ ባጭር አልቀረም፤ የሰማይ አባቱን ያስከበረ ወርቃማ ፍጻሜ አገኘ፡፡ የሕይወትን ዋና ጥሪ ለመፈጸም ጊዜን በጥበቡ የመጠቀም ጉልህ አርኣያ ሆነ፡፡ ስሙ ይክበር፡፡ ቻርልስ ሁሜል የተባለ አስተዋይ ጸሐፊ “The Tyranny of the Urgent” ብሎ የጻፈውና ቁምላቸው ፈንታሁን የተረጎመው አንድ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፡፡

/ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፣ያልተጠናቀቁ ሥራዎች፣ ምላሽ ያልተሰጣቸው ደብዳቤዎች፣ ያልተጎበኙ ወዳጆች ያልተጻፉ መጣጥፎችና ያልተነበቡ መጻሕፍት ይታዩናል፡፡ በሥራ እየባተልን ቢሆንም ጊዜ የምናገኝበት ደስታ እያደር የመነመነ ነው፡፡ ሆኖም ችግር የሚፈጥርብን ተግቶ መሥራት ሳይሆን ጥርጣሬና መወላወል ናቸው፡፡ ትልቁ አደጋ ለአስቸኳዩ ጉዳይ መላ ለመፈለግ ስንጣደፍ ዋነኛውን ጉዳይ መዘንጋቱ ነው፡፡ ችግሩ ደግሞ ዋነናው ጉዳይ ዛሬ ወይም በዚህ ሳምንት ይሠራ የሚያሰኝ አጣዳፊነት የሌለው መሆኑ ነው፡፡ ፈጣን ርምጃ የሚጠይቁን አጣዳፊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በጊዜው በጣም አስፈላጊና ወደ ጎን የማይባሉ ስለሚመስሉን ጉልበታችንን ይመጡታል፡፡ ክርስቲያን ፋታ ወስዶ መንፈሳዊ ሁኔታውን በመፈተሸ፣ የሥራ ኀላፊነት ለመቀበል እንዳይችል ሆኖ በሥራ ከተጠመደ፣ ለአስቸኳዩ ጉዳይ ምላሽ ለመስጠት ሎሌ ያድራል፡፡ በራሱና በሌሎች ዐይን ዋጋ የሚሰጠው የሚመስል ነገር፣ ሌት ተቀን ሠርቶ ማከናወን ቢችልም፣ እግዚአብሔር ያቀደለትን ሥራ ግን ሳያጠናቅቅ ይቀራል/

እንግዲያው በባርነት ቀፍድዶ የያዘን “አስቸኳይ” የሚባል አምባ ገነን የፍዳችን አንዱ ዋና ምክንያት መሆኑ ነው፡፡ አስቸኳዩን ከዋናው ጉዳይ እንዴት እንለያለን? የሚለው ጥያቄ ብርቱ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ መልስ ካገኘን የፍልሚያው እምብርት ታወቀ ማለት ነው፡፡

ይረዳን እንደ ሆነ እስቲ መላ ልምታ፡፡ በጎ ትብብራችሁን ስጡኝና ይህን ጥያቄ በጥሞና መልሱልኝ “ለመሞት አንድ ወር ቀርቶሃል የምትሠራውን ሁሉ በነዚህ ሠላሳ ቀናት ጨርስ” ብትባሉ ቀኖቹንና ሌሊቶቹን ምን ታደርጉባቸው ነበር?

ብጣሽ ወረቀት አውጡና የምታደርጓቸውን ነገሮች በቅደም ተከተል ጻፉዋቸው፡፡ ልምምዱ ምናልባት ዋና የምትሉትን ዋና ካልሆኑት ለመለየት ይረዳችሁ ይሆናል፡፡

የሕይወታችሁ ዋና ዓላማ ምንድን ነው? የደም ግፊታችሁን እየጨመረ፣ ናላችሁን እያዞረ፣ ተንፋሽ አሳጥቶ የሚያስሮጣችሁን ነገር ሁሉ ከዚህ ዋና ዓላማ አንጻር ፈትሹት፡፡ ወደ ዓላማው የሚፈስ ነባር ወንዝ ነው ወይስ በየመስኩ የፈነዳ መድረሻው ያልታወቀ የውሃ ምንጭ? የክርስቶስ ተከታይ ዋና ዓላማ ምንድን ነው የተባለ እንደሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ ባጭሩና በግልጽ ከተናገረው ከዚህ ጥቅስ የተሻለ መግለጫ አላገኘሁም፡፡ “አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፣ እንግዲያውስ ሁሉ ሞቱ በሕይወትም ያሉትም ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ፡፡” 2ኛ ቀሮ 5፡13

የክርስቶስ ተከታይ ግለ ሰብም ሆነ ማኅበረ ሰብ የሕይወት ዓላማው ንድፍ ተሠርቶለት አልቋል፡፡ የምንሠራው ሁሉ የምናስበው ሁሉ የዚህ ዋና ንድፍ (Master Plan) አካል ካልሆነ ሕገ ወጥ ግንባታ ነው፤ ለፍቶ መና ነው፡፡ እያንዳንዱዋ የእንቅስቃሴ ቅንጣት መፈተሸ ዋጋዋም መተመን አለባት፡፡ መሮጥ ብቻውን ዋጋ ቢስ ነው፤ ሕይወት መሮጫ ግብ ይሻል፤ ግቡም በአንጻሩ የመገስገሻ መስመር አለው፡፡ ሐዋርያው ትንፋሽ ሊሰበስብ ሲቃረብ ሩጫ ጨረስኩ ሳይሆን ‹‹ሩጫውን ጨረስኩ›› ማለቱ የተሰመረ መንገድ፣ የሚደረስበት ግብ መኖሩን ሲያመለክተን ነው፡፡

የቢዚነት ጉዳይ ግን ከዓላማ አንጻር ብቻ ሳይሆን በጊዜ አስተዳደር አንጻርም ሊታይ ይገባል፡፡ ጊዜ ከፈጣሪ የተሰጠን ሀብት ነው፡፡ ጊዜ ሀብት ከሆነ እንግዲያው እያንዳንዳችን “መጋቤ ጊዜያት” ሆነን በዚህ ሀብት ላይ ተሹመናል፡፡ የጊዜ መጋቢነት እንዴት ይከወን ስንል ባለ ሙያዎች ከሚመክሩን መካከል ሦስቱን ብቻ ልጥቀስ፡-

ጊዜዬ የት ጠፋ? ምን አደረግሁት? እያልክ የምትጠይቅ ከሆነ ሥራዬ ብለህ የዕለት ዕለት እንቅስቃሴህን ለተከታታይ ሰባት ቀናት ያደረግከውን ነገር ስም እየሰጠህ ልትጽፈው ትችላለህ፡፡ ከሳምንቱ በኋላ የጊዜ አጠቃቀምህን በዐይነቱ ስትሰድረው ጊዜህ ምን ላይ እንደዋለ የጊዜ ምጋቤ ባህርይህን ትረዳዋለህ፡፡ ያኔ ያላግባብ የባከነ ወይም በቂ ጊዜ ያልተሰጠው ምን እንደሆነ ግልጽ ይሆናል፡፡

ይህ የጊዜ ውሎ ግምጋሜ ወደ ሁለተኛው ዋና ነገር ይመራሃል ይህም ጊዜህን የሚሰርቁ የጊዜ መንታፊዎቸን ለይቶ ማወቅ ነው፡፡ ከታወቁት የጊዜ መንታፊዎች መካከል፡-

መወላወል (የቱን ላንሳ የቱን ልጣል)

ዝርክርክነት (ካርዱን የት ነበር ያደረግኩት)

መግቻ የሌላቸው የስልክ ጥሪዎች

ነገ ይደርሳል እያሉ መሳነፍ

ተራ/ወረፋ ጥበቃ

ጥድፊያ (ጥድፊያ ሲበዛ ፍጥነት ይቀንሳል ይባላል)

ድንገት የሚከሰቱ መስተጓጉሎች ይገኙበታል፡፡

እነዚህን የጊዜ ሌቦች እንዴት ነቅተህ እንደምትጠብቅ ከራስህ ጋር ተመካከር፡፡

ሦስተኛው ርምጃ ለሕይወትህ ዓላማ መሳካት የሚረዳ ከአንተ ባህርይና ሁናቴ ጋር የሚጣጣም የጊዜ ሰሌዳ መንደፍ ነው፡፡ የጊዜ መርሃ ግብር እንደሚያወጡት ቀላልነት ሳያዛንፉ መከተሉ ቀላል አይደለም፡፡ ላወጣኸው የጊዜ ሰሌዳ መገዛት ቢያቅትህ እንደገና መከለስና ማሻሻል ምንም ነውር የለበትም፡፡

ይህን ሁሉ ስታደርግ ልብ ማለት የሚገባህ ሕይወት ሥራ ብቻ÷ የግል ኑሮ ብቻ እንዳይደለ መገንዘብ ነው፡፡ የሥራና የዕረፍትን ሚዛን፣ የግልና የማኅበር ኑሮን ሚዛን፣ የዕለቱንና የዘላለሙን ሚዛን የሚጠብቅ የሕይወት ስልት መቀየስ ሁሉ ጎናዊ ስምረት እንዲኖረን ይረዳል፡፡

ወገኖቼ ጤናችን እስኪዛባ ደስታችን እስኪጠፋ ቢዚ ከሆንን እየቆየ ወደ ክስመት (burn out) ልንሄድ እንችላለን፡፡ በእምነት እጦት ሰበብ ሩጫ ያበዙትን ሕዝበ እስራኤል እግዚአብሔር እንደገሰጻቸውና እንደመከራቸው እኛንም ያስጠነቅቀናል፡፡

“የእስራኤል ቅዱስ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና

በመመለስና በማረፍ ትድናላችሁ፣ በፀጥታና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል፡፡” (ኢሳ 30፡15)