ደምን የሚቀይጥ ኪዳን !

ትዳር “ት/ቤት ነው” የሚሉ ብዙዎች ናቸው። ከሰው ጋር ተጣምዶ መኖር በየዕለቱ የሚማሩበት ተቋም እንጂ ሁሉን አውቆ ጨርሼዋለሁ የማይባል መሆኑን ሲያሰምሩበት። በእድሜም ይሁን በምሁርነት ታውቆ የማይጨረስና የማይመረቁበት የትምህርት ተቋም መሆኑን ለተረዱ ሁሌም በዝግጁነትና በትሁት የተማሪነት መንፈስ ለመኖር ይጠቅማቸዋልና፣ ትዳርን ት/ቤት ማለታቸው ጥሩ ብለዋል ። የመማር ልብ የሌለው ሰው ደግሞ ለመሻሻል በሩን ከመዝጋቱ ባሻገርም እውቀት በቅቶኛል ሲል የፍሬያማነት እድሉን ያጠባል። ለሚማርበት ሰው ግን ትዳር በየዕለቱ የማደጊያ ስፍራ ነው።

ትዳር “ስራ ነው” የሚሉት ደግሞ፣ መልካሙን የትዳር ፍሬ ለመብላት እድል የምትቸረው ሳይሆን ተግቶ መስራት ግዴታ መሆኑን ማስረገጥ ይፈልጋሉ። በድካምና በትናንት ውድቀት ላይ ከማተኮር ይልቅ ትዳር ከተሰራበት አድጎና ጎልብቶ ፍሬያማ ነገን ማየት ያስችላልና፣ ትዳርን በስራ መመሰላቸው መልካም ብለዋል። እውነትም፣ ግጭቶች ከተሰራባቸው መማሪያዎች፣ ውድቀቶች ከተሰራባቸው ተመክሮዎች፣ ድካሞች ከተሰራባቸው ብርታቶች ይሆናሉና፣ ትዳር “ስራ” መሆኑ የገባቸው የጣፈጠ ጎጆ ከፊታቸው አለ።

ትዳር “ቀንበር ነው” የሚሉም አሉ። እንደ ግል ፈቃድ መኖር የሚያበቃበት ብቻ ሳይሆን ሸክምንም የሚጋሩበት ሃላፊነት መሆኑን ሲያብራሩ። ሃላፊነቱን የተረዳ ሰው አጋሩ ላይ ከመጠቆም ይልቅ እራሱንም እንዲያይ፣ ሌላውን እየከሰሰና እያማረረ ከመኖር ባሻገር በእራስ ላይ የማተኮርንም እድል ይሰጠዋልና የትዳርን ሃላፊነት መረዳት ታላቅ ማስተዋል ነው። ሃላፊነቱ ደግሞ ከግልና ከቤት ያለፈ የትውልድ ሃላፊነት ነው። በተለይ በዚህ ክፉ ዘመን፤ ልጆች ጥበብን ሊቀስሙ ከሚላኩበት ትምህርት ቤት፣ የጥበብ ሁሉ ራስ በሆነው በእግዚአብሔር እንዲያምጹ ለጋ አእምሮአቸው ይበረዛል። ከቤታቸው ሳይወጡ በኤሌክትሮኒክ መገናኛ ብዙሃን ክፋት ይዘራባቸዋል። ታዲያ ሰው ሁሉ ቤቱን በሃላፊነት ቢያስተዳድርና በእግዚአብሔር መንገድ ቢኖር ትውልድና ሃገር ምን ያህል ባረፉ ነበር።

“ትዳር እድል ነው።” የሚሉም አሉ። እነሱ ደግሞ ትዳር በለስ የቀናቸው፣ እድል የሰመረላቸው የሚያገኙት የእጣ ችሮታ ነው ብለው ያምናሉ። ታዋቂው ፈላስፋ ሶቅራጥስ መልካም ትዳር የእድል ውጤት ነው፤ ብሎ ያስብ ነበርና “እድለኛ ከሆንክ መልካም ትዳር ታገኛለህ፣ እድል ከጠመመብህ ደግሞ ትዳር ፈላስፋ ያደርግሃል” ማለቱ ተዘግቧል። ትዳሬ ከፍቶብኝ ፈላስፋ ሆንኩ ከማለቱም ባሻገር ለትዳራችን አለመሳካት ሃላፊነቱ የእኔ ሳይሆን የእድል ጉዳይ ነው፤ ማለቱም ነው። ይሄኛው አስተሳሰብ ከስህተትነቱም በዘለለ ሃላፊነትን የማይቀበል ትውልድ ይቀርጻልና አደገኛ አስተሳሰብ ነው። ገበሬ “ፍሬያማ እርሻ የእድል ውጤት ነው” ቢል ረሃብ በነገሰ ነበር። ውርጩን ተጋፍጦ ባላረሰ፣ ምቾቱን ሰውቶ ባልደከመ፣ በተስፋ ዘርቶ፣ በጽናት ኮትኩቶ፣ በትጋት ባላጨደ ነበር።. ሰዎች ትዳርን የሚገልጹበት ብዙ መንገድ አለ።

የዚህች አጭር ጽሑፍ ዓላማ ግን “ትዳር ቃልኪዳን ነው።” ለማለት ነው። ያውም ከሰው ጋር ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔርም የሚገኝበት የከበረ ቃል ኪዳን። ቃሉ ከምታልፍ ግዙፉ ሰማይና ምድር ቢያልፉ የሚቀሉት እግዚአብሔር ደግሞ ቃል ኪዳንን ያከብራል። ስለዚህም ነው በዘመናት ሁሉ በቃሉ የታመነ፣ ቃልኪዳኑንም የሚፈጽም አምላክ ከኪዳኑ ጋር የቆመው። ክርስቲያናዊ ትዳርም የአንድ ወንድና የአንድ ሴት ጉዳይ ብቻ አይደለም። ይልቁንም አንድ ወንድና አንድ ሴት በአምላካቸውና በትዳር ፈጣሪ በእግዚአብሔር ፊት የሚያደርጉት የእድሜ ልክ የቃል ኪዳን ጥምረት እንጂ። ስለዚህም እግዚአብሔር አንዱ የቃልኪዳኑ አባል ነው። በትዳር ቃል ኪዳናቸው ጸንተው ከሚቆሙት ጋር ሁሉ ይቆማል። “…ሚስትህ ባልንጀራህና የቃል ኪዳንህ ሚስት ሆና ሳለች እርስዋን አታልለሃታልና እግዚአብሔር በአንተና በልጅነት ሚስትህ መካከል ምስክር ስለ ሆነ ነው።” ትንቢተ ሚልክያስ 2፡14

በዚህ መረዳት ስናየው ትዳርን በሙላት የሚገልጸው “ቃል ኪዳን” የሚለው ስያሜ ነው። ቀጣዩ ጥያቄ፣ ቃል ኪዳን ምንድነው?” የሚለው ይሆናል። “ትዳር ቃል ኪዳን ነው። አንድ ሲደመር አንድን አንድ የሚያደርግ ቃልኪዳን።

To Read the full Article on Berea Magazine 2016 Click here

To read the