(የዮሐንስ ራእይ ምዕ. 22)
———-
10፤ ለእኔም። ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።
11፤ ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ።
12፤ እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።
13፤ አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።
ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔርን በመፍራት ያገለገሉ በእግዚአብሔር ፊት በጽድቅ እየኖሩ እግዚአብሔርን እየፈለጉ በጎነቱን ለትውልድ በቃል በኑሮና በተግባር በማሳየት የተጉት ቅዱሳን የእግዚአብሔር ሰዎች ስለ እምነታቸው ሰለከፈሉት ታላቅ ዋጋ ስለሚቀበሉት ብድራት በዚህ ዘመን ቢኖሩ ምን ይሉን ይሆን?
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በጣም ከሚያስፈሩት ጥቅሶች ሁሉ ዘመንን ያለዋጋ ስለሚያጥናቅቁ ወይንም ዋጋቸውን በምድር ተቀብለው በሰማይ ምንም ዋጋ ስለማይቀበሉ ሰዎች የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው። በተለይም ሮጠው ሮጠው ብዙዎችን አስከትለው ተከታዮችንም አብዝተውና ራሳቸውን አሳይተው ጌታን ለእንድም ደቂቃ እንኳን ሳያሳዩ እራሳቸው እንደታዩ ፥ የእነርሱን ነገር ሲያሳዩ የከረሙ ሰዎች ስራቸው መቃጠሉ እና ደግሞም ” አላውቃችሁም ” መባላቸውን ሳስብ እጅግ በጣም ያስፈራኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ የእያንዳንዳችን ዋጋ በእጁ መኖሩ እና ጌታም በኋለኛው ዘመን ለእያንዳንዱ ሰው ብድራቱን እንደስራው መጠን መክፈሉን ሳስብ የሚያበረታታኝ ነገር ሆኖ ይሰማኛል። ወገኖቼ ሰውን ደስ አሰኝታችሁ አለሙን አሰደምማችሁ ዛሬ ዓለምን ያስደመማችሁበት ነገር ጌታን የሚያሳዝን ከሆነ ልትፈሩ እና ልታዝኑ ይገባችኋል።
ማንኛውም ጌታን የሚያገለግል ሰው ብድራቱን ከሚከፍለው እጅ ደሞዙን ለመቀበል የተዘጋጀ ሰው መሆን አለበት። ዛሬ ዛሬ በተለየየ መንገድ ወንጌል እንሰብካለን ብላችሁ የምትሉ ሰዎች ዋጋችሁን ተምናችሁ ዋጋችሁን ከሚከፍለው ጌታ እጅ ለመቀበል እንጂ በምንም ምክንያት የምታደርጉትን ነገር አታድርጉት። የምንሮጠው ሩጫ ሁሉ ምን ለማግኘት እና ከማን ምን ለማግኘት እንደምንሮጥ ልብና ኩላሊትን የሚመረምረው ጌታ ሁሉን ያውቃል።
ለዝና ከሆነ ከእኛ የተሻሉ ዝነኞች መኖራቸውን እንርሳ፡ ለክብር ከሆነ ደግሞ በሰው ሚዛን ከእኛ ይልቅ የከበሩ ሰዎች መኖራቸውን አንርሳ። ለሃብትና ለባለጠግነት ከሆነ ድግሞ ለዚህ የሚሮጡ የማይደረስባቸው ባለጠጎች እንዳሉ አንርሳ። የምናደርገውን ሁሉ ለእርሱ ክብርና ለመንግስቱ መስፋት እናድርገው። ያን ጊዜ ትክክለኛ ብድራታችንን ከጌታ ከኢየሱስ እጅ እንቀበላለን።
እኔ በጣም በጣም የሚያስደንቀኝ ነገር የእነርሱ ሥራ በእግዚአብሔር ፊት ሚዛን ማግኘቱን ሳያውቁ የመንገስተ ሰማያትን ሚዛን የጨበጡ የሚመስላቸው ሰዎች አሉ። ለራሳቸው ከምንም በላይ የተለየ የሚመጻደቁብት ሰራ ሰራን ብለው የሚሉት ነገር እንዳላቸው ማውራታቸው ነው። በእግዚአብሔር ስም እግዚአብሔርን እግዚአብሔርን ራሱን ለምስክርነት ስለ ስራው እንዲሰጥ ሲጠይቁ ወይንም ሲናገሩ ይታያሉ። እባካችሁ እንመለስ። መመለስ በጣም ይጠቅመናል። እውነትን ማስተማር ማለት የዳኝነትን ሥፍራ መያዝ ማለት አይደለም። የእግዚአብሔር እውነት ፍጹም ነው። ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን እውነት ሳይሆን የእኛን የሆነውን መረዳት ነው እውነት ብለን የምናስተምረው። ለዚህም ደግሞ ዋጋ እንከፍላለን። ያገለገልነው አገልግሎት ሁሉ ለእግዚአብሔር ክብርና ለቅዱሳን ድግሞ እረፍትና አምላካዊ ሰላምን የማይሰጥ ከሆነ ይህ የሚቃጠል ስራ ነው የሚሆነው።
የክርስትና ሃይማኖት በምድር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እያሌ ሰዎች የእግዚአብሔርን እውነት ተረዳን ባሉት መልኩ ለማስተማር ሞክረዋል። ነገር ግን እነኝህ ያስተማሩ ወይንም ያገለገሉ ሰዎች ሁሉ እውነተኞች ናቸው ማለት እና ስራቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል ማለት እይደለም። ለሁሉም ግን እንደስራው የሚክፍል ጌታ በጊዜው ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ስራው መጠን ዋጋውን ያስረክበዋል።
ዛሬ ይህንን ለመጻፍ ያስገደደኝ ታሪክ ወንጌልን በማገልገል ህይወታቸውን ሰለሰጡ ሰዎች በማሰላስል ላይ እያለሁ በውስጤ የመጣውን ሃሳብ ላካፍላችሁ ብዬ ነው። እነ ጳውሎስን እነ ጴጥሮሰን እነ ዮሐንስን እነ ያዕቆብን እነ እስጢፋኖስን አሰብኳቸው። በዚህ ዘመን በምድር ላይ ቢኖሩ ምን ይባሉ ይሆን? ብዬ አስብኩ። ዋጋቸውን ሳስብ ምድር እንዳልተገባቸው በመንከራተት በብዙ ነቀፌታ በብዙ መከራ በብዙ ስደት ፡ በውስጥ ፍርሃት ፣ በውጭ ፍርሃት፡ በወንድሞች ፍርሃት በውጭ ባሉት ዘንድ ፍርሃት። በውሸተኛ ወንድሞች ፍርሃት። በብዙ ግርፋት ፡ በብዙ እስራት እንቅልፍ በማጣት በብዙ ድካም ፡ በመዞር ከሀገር ሀገር በመንከራተት በወርደት ሁሉ ተፈተኑ አለፉ። የምድርን ትርፍ ንቀው ከክርስቶስ ጋር መከራን መቀበልን መረጡ። ለተጠሩበት ነገር ዋጋ ሰጥተው ብድራታቸውን ትኩር ብለው ዋጋቸውን የያዘውን ጌታ ስላዩት የምድር አጀብ እና ጎሽ ባይነት ሳያታልላቸው ሩጫቸውን ፈጸሙ።
ዋጋቸው በእርግጥ እንደሚጠብቃቸው ያውቁ ነበርና ያንን ትኩር ብለው ተመልክተው ለዚያ ሮጡ እይናቸው በላይኛው ላይ እንደፈዘዘ ብድራታቸውን ሲያስቡ ከእርሱ እንደሚቀበሉ እያዩ የማይጠፋውን አክሊል (1ኛቆሮ9፥24-25)፣የደስታን አክሊል (1ኛተሰሎ2፥19)፣የጽድቅን አክሊል 2ኛጢሞ4፥8)፣የክብርን አክሊል(1ኛጴጥ 5፥4) እና የህይወትን አክሊል(ራዕ2፥10) ለመቀበል በእርሱ ዘንድ ይህ እንደሚጠብቃቸው ስላመኑ ይህንን ለመቀበል ሮጡ ሩጫቸውንም በዚህ ጨረሱ።
በምድር የምናገኘው ነገር ሁሉ የሚዝግ የሚበሰብስ እና የሚቃጠል መሆኑን አንዘንጋ። ሁሉም ነገር እንደ ሳር አበባ ነው። ዛሬ ታይቶ እንደሚጠወልግ ቅጠል ነው። ሁሉም ነገር የሚዝግ ነው የሚበሰብስ ነው ምድራዊ ነገር ሁሉ የሚያረጅ እና የሚጠፋ ነው ። ሰለዚህ ነው ጌታ ኢየሱስም መዝገባችሁ በላይ ይሁን አለ። መዝገብ ቀርቶልን ይሆን? ብል በማይበላው ዝገት በማያገኘው በጌታ ዘንድ ይሆንልን ይሆን ? ወይንስ ሩጫችን እዚሁ ከብረን እዚሁ ከብደን እዚሁ የሚቃጠል ይሆን? ስለዚህ ለሚጠፋው ክብር ለሚሻርው ስምና ዝና ዝገትና ብል ለሚበላው ሃብትና ባለጠግነት መሮጥ አቁመን የምይጠፋውን እና የማይበላሸውን አክሊል ለመቀበል እንትጋ/ማቴ6፥19/። “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፥ እድፈትም ለሌለበት፥ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ፤ ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።”
(1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 1:3-5)።
እውነተኛ ደስታችን መመስረት ያለበት ጌታችን በመምጣቱ እና ለምንጠብቀውም ሰዎች ዋጋችንን እንደሚክፍል በመረዳቱ ላይ ነው። የእኛ ደስታ ሊሆን የሚገባው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው። የደስታውን ምንጭ ጌታውን የደረገ ሰው በምንም በሌሎች ነገሮች መደስት አይመቸውም።
የደስታን አክሊል ለመቀበል የተዘጋጀ ሰው ምድራዊ ደስታ አይነጥቀውም። የደስታን አክሊል እንደሚጎናጸፍ ያውቃል። ጌታን በማግኘቱ ብቻ በለቅሶ ፈንታ የደስታን ዘይት አምላኩ ቅብቶታል። ዋጋችንን የሚያሳጡን ነገሮች ምድራዊ የሆኑ እና ደስታችንን እናገኛለን ብለን የምንደገፍባቸው ነገሮች ናቸው። “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፥ ደስ ይበላችሁ“ (ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 4:4)። ጳውሎስ ለፊልጵስዮስ ሰዎች ይህንን ሲጽፍ ከጌታ ውጭ ምንም ደስታ የሚያመጣላቸው ነገር እንደሌለ ስለሚያውቅ ነው።
የጌታ እውነተኛ ደስታ ዕንባ ከእይናችን ለዘላለም የሚወገድበት ደስታ ነው። ሃዘንን ያስወገደ ጌታን ኢየሱስን በማወቅ ላይ ብቻ የተመረኮዘ ደስታ ነው። ይህ ደስታ በመብልና በመጠጥ ያልሆነ ደስታ ነው።
ራዕ21፥4 “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ። ሃዘን ሞት ጩኸት የተወገደበት ደስታ ነው።
ይህ ደስታ ሃዘን የሌለበት መርገም የሌለበት ፡ ሌሊት ወይንም ጨለማ የሌለበት ደስታ ነው። ስለዚህ ፍጹም የሆነን ደስታ ሊያጎናጽፈን ነው ጌታ የጠራን። ስለዚህ መጠንቀቅ ይገባናል። ለምድራዊ ደስታ ብለን የተጠበቀልንን ሰማያዊ ደስታ እንዳናጣ እንጠንቀቅ።

እንግዲህ ሁላችንም ከጌታ እጅ ብድራታችንን ለመቀበል እንትጋ ትርፍ በሚገኝበት ነገር ተጠላልፈን እንዳንገኝ እንጠንቀቅ።

ጌታ ኢየሱስ ለሁሉም እንደ ስራው መጠን ይክፈለው ዘንድ ዋጋው በእጁ አለ!!!!

ጌታ ይባርካችሁ!!!
ይቀጥላል!!!!
መጋቢ መስፍን ሹጌ(ዶ/ር