መልካም ስራ-ደግነት    ምንጭ አንድ የፌስቡክ ወዳጄ (Written in english)
በአንድ ዘመናዊ ቄራ ድርጅት ውስጥ የምትሰራ ሴት ነበረች። ከእለታት በአንድ የአርብ እለት ቀኑን ሙሉ በስራ ላይ ስትባዝን ውላ አመሻሽ ላይ መደበኛው የስራ ሰዓት ተከውኖ ሰራተኛ ሁሉ ወደየቤቱ መሄድ ሲጀምር እርሷም ለመጨረሻ ጊዜ የዕለት ስራዋን ለመሰናበት በቀዝቃዛው የሥጋ ማቆያ ክፍል ውስጥ ያለውን ሁኔታ ለማየት ገባች።
ወደ ውስጥ እንደዘለቀች በሩ በድንገት ተዘጋ። በፍጥነት ወደበሩ አምርታ የበሩን እጀታ ብትፈልግ በስፍራው የለም! ምናልባት ተነቅሎ ወድቆ እንደሆን በማለት በጨለማው የማቀዝቀዣ ክፍል ወለል ላይ ተንበርክካ ወለሉን ማሰስ ጀመረች። ምንም ነገር የለም።ደነገጠች። ምናልባት ከስራ ያልወጡ የስራ ባልደረቦቿ ቢሰሙኝ በማለት በሩን ባለ በሌለ ሀይሏ መደብደብ ጀመረች። ለእርዳታ የመጣ አልተገኘም። ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ጮኸች። የክፍሉ የገደል ማሚቱ ድምፅዋን መልሶ ከማስተጋባቱ በቀር የሰማት የሰው ዘር አልነበረም። ተስፋ በመቁረጥ በጨለማው የማቀዝቀዣ ወለል ላይ ተኮራምታ ቁጢጥ አለች። በተስፋ ቢስነት ስሜት ማልቀስ ጀመረች። ቅዝቃዜው ሥጋዋን አለፎ አጥንቷን እንደመርፌ ይጠቀጥቃት ጀመር። ሰዓታት አለፉ። ደሟ በሰውነቷ መዘዋወር ያቆመ መሰላት። እጆቿንና እግሮቿን ማንቀሳቀስ ተሳናት። ከዚህ ሁሉ በኋላ እራሷን ስታ በቀዝቃዛው ክፍል ወለል ላይ ተዘረጋች።
የግቢው ጠባቂ ያለልማዱ በቢሮዎች አካባቢ እየተዘዋወረ በየመስኮቶቹ አያጮለቀ ይመለከታል። ጆሮውን በበሮች ላይ ለጥፎ እንግዳ ነገር ለማዳመጥ ይሞክራል።ምንም አዲስ ነገር የለም። በየቢሮዎቹ ሁለት ሶስቴ መለስ ቀለስ ብሎ ካየ በኋላ ተመልሶ ለመሄድ መራመድ ጀመረ። አካሄዱ እንዳመነታ ሰው እግሮቹን እየጎተተ ነበር። በዚያ መሀል ወደ ቀዝቃዛው ክፍል ዓይኖቹን ወረወረ። አንዲት ብራማ ቀለም ያላት ብረት የመብራት ብርሃን እያንፀባረቀች ስትብረቀረቅ ተመለከተ። በፍጥነት ወደ ክፍሉ አመራ። እጀታውን ይዞ ለመክፈት ሲሞክር ውልቅ ብሎ እጁ ላይ ቀረ። መልሶ አስገባውና ከፈተው። አንዲት በሞትና በህይወት መካከል ያለች የሴት አካል ታየው። በፍጥነት ከወደቀችበት አንስቶ እርዳታ ወደምታገኝበት በማድረስ ከሞት ታደጋት።
ይህም ጉዳይ በመስሪያ ቤቱ ትልቅ መነጋገሪያ ሆነ።ሴትዮዋም ወደስራ በተመለሰች ጊዜ የጥበቃውን ሰው ለማመስገን ወደ እርሱ ሄደች። ከምስጋናዋ በኋላ ስለገጠመኙ የበለጠ ለማወቅ በምን አጋጣሚ ወደ ማቀዝቀዣው ክፍል እንደሄደና እንዳዳናት ጠየቀችው።
ምላሹም እንዲህ ነበር፦
“በዚህ ድርጅት ለብዙ ዓመታት አገልግያለሁ።ብዙዎች ሲመጡ ተቀብዬ ሲሄዱ ሸኝቻለሁ። ያ ሁሉ ሺህ ሰው በዚህ ደጃፍ ሲገባና ሲወጣ ከቁም ቆጥሮ የግዜር ሰላምታ የሚሰጠች ጥቂት ነው። ዛሬ ለልምዱ ሰላም ያለኝ ነገ ይዘነጋኛል። ከዚያ ሁሉ መሃል ግን አንድም ቀን ሳታጓድል ስትወጣና ስትገባ በፈገግታ ሰላምታ የምትሰጠኝ ሴት ነበረች። እርሷን ሳይ ሰው እንደሆንኩ ይሰማኛል። ሁሌም በምታሳየኝ ሰብአዊ ክብር የማደርግላት ባይኖረኝም አምላክ ከክፉ እንዲጠብቃት የዘወትር ፀሎቴ ነበር። አንድ ቀን በፈገግታ ሰላምታ ሰጥታኝ ስራ የገባችውን ሴት ሰራተኛው ሁሉ ሲወጣ ሳላያት ቀረሁ። በሰላም ብትወጣ ሳትሰናበተኝ እንደማታልፈኝ እርግጠኛ ነበርኩ። ውስጤ ተረበሸ። ምናልባት ከቢሮዋ ቆይታ እንደሆን ለማጣራት ሄድኩ። የለችም። እግሬ ለመመለስ ቢሄድም ልቤ ግን እምቢ አለኝ ወደ አንድ ጎን ሳማትር ያችን የምታብረቀርቅ የቆልፍ ማንጠልጠያ ተመለከትኩ። ያቺ ስፈልጋት የነበረች ሴት አንቺ ነበርሽ። እግዜር በዚህ መልክ ውለታሽን እንድከፍል ፈቅዶ ኖሩ ከሞት ታደግሁሽ።

“ልጄ እኔ ምክንያት ሆንኩ እንጂ ያዳነሽ መልካም ሰብአዊነትሽ ነው ሲል አከለበት ።

መልካም ስራ የ እለቱ መነጋገርያ ርዕሳችን ይሆናል። እምነት ያለ ስራ ሙት ነው።ያዕቆብ 2:20 አንተ ከንቱ ሰው፥ እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን?