ጊዜው ለክርስትያኖች የሚመች አልነበረም። በከተማው ውስጥ ጴንጤን የማያባርርና የማያወግዝ አልነበረም። ከባድ የስደት ጊዜ ነበር። አንዴ ረገብ አንዴ ደግሞ ሳይታሰብ እየተቀጣጠለ የሚነሳው ስደት በክርስትያን አማኞች ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል። አንዳንዶች ከስደቱ አሰቃቂነት የተነሳ ከተማዋን ለቀው ወጥተዋል። ቤተክርስትያን ተቃጥሏል። በርካታ ቅዱሳን ያለ ህግ በየተገኙበት እየተደበደቡ ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል። በዚህ ሁሉ ከባድ መከራና ስደት ግን የእግዚአብሄር ጥበቃ ስለበዛላቸው አንድም ሰው እንኳን ከመካከላቸው አልሞተም። እንደውም ስደትና መከራው ለአንዳንዶች ወደ ጌታ ይበልጥ መቅረቢያ ሆኖላቸዋል።
በዚህ ምክንያት ታደሰ በጾምና በጸሎት ጌታ ፊት ቆይቶ ነበር ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ከተማ የወጣው። አሁን ሁሉም ነገር ጋብ ብሎ የተረጋጋ ይመስላል። ታደሰን በከተማው ሁሉ በጴንጤነቱ የማያውቀው የለም። ዓለማውያን ሲጠሩት “አባ መናፍቅ” ይሉታል። የመናፍቃን አባት ማለታቸው ነው።
ታደሰ ከጾም ጸሎት የቤት ውስጥ ቆይታው ገና እንደወጣ በመጀመርያ ያገኘው ድሮ በልጅነቱ አብሮ አደጉ የነበረችውንና ከሃያ አምስት አመት በፊት የተለያትን ጸደይን ነበር። በልጅነታቸው በጣም ይዋደዱ ነበር። ጸደይ እንዳየችው ታዴ ብላ አንገቱ ላይ ተጠመጠመችበት። ታዴም በደስታ አቅፎ ሳማት። ደህንነታቸውን ተጠያይቀው ሲያበቁ ታዴ ምሳ ልጋብዝሽ ብሎ ይዟት አቅራቢያቸው ወደ አለው ሆቴል ጎራ አሉ። ጸደይ ደህንነቱን ደጋግማ ከጠየቀችው ሁዋላ ታዴም መልሶ “ለመሆኑ ይህን ያህል ጊዜ የት ነበርሽ?” በማለት ጠየቃት። ጸደይ ትካዜና ሃዘን ገባት። እንደ ምንም ብላ መናገር ጀምራ ያለ የሌለ አሳዛኝ ታሪኳን ደረደረችለት። ከሃገር ወጥታ ዱባይ በሚባል ከተማ ሴተኛ አዳሪ ሆና ለገንዘብ ስትል ስንት መከራ እንደከፈለችና በመጨረሻም ገንዘቧን ሰብስባ ወደ ሃገሯ ስትመለስ ያላትን ሁሉ በሌባ ተዘርፋ ባዶ እጇን ወደ ሃገሯ እንደተመለሰች በለቅሶ ተረከችለት። ድካምዋ፣ ልፋትዋ፣ መዋረድዋ፣ ባዶ ዋን መቅረቷ፣ወደ አእምሮዋ እየመጣ ሁልጊዜ እንደምትበሳጭና ይበልጡን ደግሞ ያሳለፈችው የሃጥያት ዘመን በጸጸት እንደሚያንገበግባት እያነባች ነገረችው። ታደሰም “አንቺ ብቻ እንኳን ደህና ሆንሽ እንጂ ጌታ ቀሪውን ዘመንሽን ያድሳል አይዞሽ” በማለት ሊያጽናናት ቢሞክርም ጸደይ የምትጽናና አልሆነችም። ስለጌታ ሊመሰክርላት ሲሞክር ይበልጥ ያለፈችበት ሕይወትና የሃጥያትዋ ብዛት እየታሰባት አይኗን አንስታ ወደ ጌታ ማየት አልቻለችም። “ስማ እንደኔ አይነትዋን ሰው ጌታ ይቀበለዋል ብዬ አላምንም… የሃጥያቴ ጥግ እኮ እላይ ድረስ ነው… ምናልባት ብነግርህ “ዓይንሽን ያጥፋው ብለህ ነው ጥለኀኝ የምትሄደው… ስለማታውቅ ነው” በማለት አንገቷን አዘንብላ ትካዜ ውስጥ ገባች።
ሰዓቱ ስለሄደ የምሳቸውን ሂሳብ ለመክፈል ታዴ ወደ ኪሱ እጁን ቢያስገባ ምንም የለም። ያለወትሮው የገንዘብ ቦርሳውን ትቶ ነው የወጣው። ታዴ በጣም ደነገጠ… ሃይለኛ ላብ በአንድ ጊዜ አላበው… “ሌባ በልተህ ብር ረሳሁ የምትል… አጭበርባሪ፣… ቀጣፊ፣ ጴንጤ ብለው በሰበብ ሲወግሩት ታየው” ጸደይም መደንገጡን አይታ “ ችግር አለ እንዴ? ምን ሆንክ?“ ብላ ግራ በተጋባ ድምጽ ጠየቀችው። እርሱም “እባክሽን ብሩ ያለው ሌላ ኪሴ ውስጥ ነው… እቤት እረሰቼው ነው የወጣሁት ከማለቱ” ጸደይ “በወላዲት አምላክ ጉድ ሆን” አለችው። ይህን እየተባባሉና የሚያደርጉት ጠፍቷቸው ግራ ተጋብተው ሳለ አስተናጋጇ ፖስታና ሰማንያ ስድስት ብር ከሃምሳ ሳንቲም አምጥታ እፊታቸው አስቀመጠች። ታዴም በመገረም ይሄ ደግሞ ምንድነው? ሲላት “ሂሳባችሁ ተከፍሏል! መልሱንና ፖስታውንም ስጪው ተብዬ ነው ብላው ፊቱ አስቀመጠችው።
እየተገረመ ደጋግሞ ማነው? ማነው? ቢላት… እንዴ እዛ ፊታችሁ ሙሉ ነጭ ልብስ ለብሶ የተቀመጠው ሰው ነዋ… አላያችሁትም ይህንን ሲሰጠኝ?አብራችሁ ነው እኮ የገባችሁት ብላ መለሰችላቸው። ታዴ በመገረም… ከእኔ ጋር የገባ ሰው?… የአሁኑ ይባስ! ብሎ ተደናግጦ ማሰብ ሲጀምር አስተናጋጇ ትታቸው ወደ ስራዋ ተመለሰች። ሲገቡ አብሯቸው የገባም ሆነ ነጭ ልብስ ለብሶ ፊት ለፊታቸው የተቀመጠ ሰው አልነበረም። እየተገረመ ፖስታውን ቀስ ብሎ ሲከፍተው ባለመቶ ብር ኖቶችን አየ… አስር ከባንክ አዲስ የወጡ የሚመስሉ ባለመቶ ብር ኖቶችን አንድ ሺህ ብሎ ቆጠረ። መልስ ተብሎ ከተሰጠው ሰማንያ ስድስት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ጋር በድምሩ አንድ ሺህ ሰማንያ ስድስት ብር ከሃምሳ ሳንቲም… ተከፍሏል! የሚለው የአስተናጋጂቱ ድምጽ በልዩ ሁኔታ በጆሮው አስተጋባ…አይኖቹምተከፈቱ… ታዴም ዞር ብሎ በተራው ጸደይን የአንቺም ተከፍሏል! አላት። ጸደይ ደንግጣ ምን? አለች ሃጥያትሽ የከበደሽ የሃጥያት እዳሽ በሙሉ ተከፍሏል!… ልክ እኔን አስጨንቆኝ የነበረው እዳ እንደተከፈለ የአንቺንም የሃጥያት እዳ ኢየሱስ ከፍሎታል! አላት።
ጸደይ ፊቷ በአንድ ጊዜ ተቀየረ … እንባዋም በአይኖቿ ይፈሱ ጀመረ… የአስጨነቃት ሸክም ከርሷ ላይ ሲነሳ ታወቃት… ታዴም እንጸልይ ሲላት ሳታቅማማ እጁን ይዛ መጸለይ ጀመሩ። ጸደይ ንስሃ ገብታ ኢየሱስን ተቀበለች። ተከፍሏል! የሚለው ቃል በሁለቱም ጆሮ ውስጥ በድጋሚ አስተጋባ።