ክርስትያንና ፖለቲካ – በ ኮነ ፍሥሐ
ክርስትያኖች በማሕበረሰባቸው ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባውን ተሳትፎ በመገደብ የራሳቸውን መንፈሳዊ ሕይወት መገንባት ላይ ብቻ የሚያተኩሩበት ጊዜ ይታያል። በርካታዎችም የግል ኑሮአቸውን ለማሳካት ከማተኮር ይሁን የፖለቲካ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉሙን ካለመረዳት፣ ባልታወቀ ሁኔታ ራሳቸውን ለማህበረሰቡ መፍትሄና እድገት ሊያመጡ ከሚችሉ ተግባራዊ የፖለቲካና አስተዳደር ክንውኖች ራሳቸውን ሲያገሉ ማየት የተለመደ ነው። “ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ ነው” የሚለው አባባል ቅቡልነቱ በወንጌላውያን ክርስትያን ማህበረሰብ ውስጥ የጎላ ነው። በተለይም አንድ የመንግስት አካል የሚያካሂዳቸውን ጎጂ የአስተዳደር በደሎች እያዩ ዝም ማለት በክርስትያኖች መሃከል እየበዛ መምጣቱ በብዙዎች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኗል። በርካታ ክርስትያኖች መጽሃፍ ቅዱስ ስለመንግስት ስልጣን፣ ለመንግስት ስለመገዛት፣ እና ስለምድራዊ ሃላፊነታችን የተሳሳተ ግንዛቤ አላቸው። አንዳንዶች “አገራችን በሰማይ ነው” በማለት ራሳቸውን ሲያገሉ ሌሎች ደግሞ ለማንኛውም የመንግስት ትዕዛዝ በፍጹም ተገዙ ይላል በማለት ዝምታን ይመርጣሉ። የቤርያ የመጽሔት ዝግጅት ወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን፣ ዶ/ር ዓዳም ቱሉ፣ ዶ/ር ተስፋዬ ሮበሌ፣ ወንድም ንጉሴ ቡልቻና ወንድም ኮነ ፍስሃን በዚህ ዙርያ ከሰጡን ቃለ መጠይቅና በጽሑፍ ካሰፈሩት ሃሳብ ይዞላችሁ ቀርቧል።
በደቡብ አፍሪካ መጠኑ የሰፋ ጥቃት በስደተኞች ላይ ሲካሄድ የምድሪቱ ክርስትያኖች ለመቃወም እና የእግዚአብሄር ቃል ስለመጻተኞች የሚናገረውን በመናገር ድምፃቸውን ለማሰማት ድፍረትን አጥተው ታይተዋል። የደቡብ አፍሪካን አፓርታይድ ዘረኝነትን በመቃወም ቀደምት የነበረው የነ ቄስ ዴዝሞንድ ቱቱ ምሳሌነት ዛሬ ከደቡብ አፍሪካዋ ቤተክርስትያን ውስጥ ይህን ግፍ የሚቃወም ለአብነት እንኳን አልተገኘም። ከመንግስትና ከፖሊስ ቀድማ የምስባክ ድምጽዋን ልታሰማ ይገባት የነበረችው ቤተክርስትያን በደቡብ አፍሪካ ድምጽ አልባ ሆና ታይታለች።
በርካታ አገሮች ህዝባቸውን ለአመጽ እና ለርሃብ ሲዳርጉና በርካታ ዜጎቻቸውን በእስር ሲያሰቃዩ ክርስትያኖች ለሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ወይንም ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ ለማሰማት ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም። በኤርትራ፣ በኢትዮጵያ፣ በየመን፣ በሶርያ፣ በደቡብ ሱዳንና በሌሎችም በርካታ አገሮች ውስጥ ብዙ ንፁሓን በእስር ላይ ይገኛሉ። ብዙዎችም በቦምብ እና በጥይት በገዛ መንግስታቸው ሲገደሉ አያሌዎች ለስደትና ለባህር አደጋ አልፈው ተሰጥተዋል። ቤተ እምነቶችና ክርስትያኖች ከመጸለይ ባሻገር ድርሻቸው ምን ይሆን?
በዚህ ምዕተ አመት ብቻ ታይቶ የማይታወቅ የአፍሪካ ህዝብ ከመንደሩ እየተሰደደ ይገኛል። አብዛኛው ከአሰበበት ሳይደርስ በባህር እየሰጠመ ያልቃል። በተለይም ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን የዚህ አሳዛኝ የባህር መቅሰፍት ሰለባ ሆነዋል። እንደ ክርስትያን ምን አደረግን ብለን ራሳችንን እንጠይቅ? ፖለቲካ ነውና አያገባኝም ብለን ይሆን? የአደጋው ስረ ምክንያት(ROOT CAUSE) ናቸው የምንላቸውን ስረመሰረታዊ የድህነት ችግሮችን ለመቅረፍ ምን አድርገናል? ድምጻችንን ለማሰማት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ለምን ተሳነን?
የክርስትያኖች ተሳትፎ በፖለቲካ ውስጥ እስከ ምን ድረስ መሆን አለበት?ፖለቲካ ምንድነው? ክርስትያኖች ለምን ይፈሩታል? ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ የሚከተለውን መልሰውልናል:
በጎልደን ኦይል ሚኒስት(GoldenOil.org) የሚያገለግለው ወንጌላዊ ያሬድ ጥላሁን በመጀመርያ ክርስትያንና ፖለቲካ የሚሉትን ቃላቶች እንዴት በተሳሳተ መልኩ እንደምናያቸው መግለጽ እወዳለሁ በማለት ይጀምራል። ፖለቲካ በጥሬ ቃሉ ካየነው የአገር አስተዳደርና አመራር ስልት ማለት ነው። ሆኖም ፖለቲካ ለሚለው ቃል በኢትዮጵያ ውስጥ ለቃሉ የሚሰጠው ትርጓሜና እዚህ አገር የሚሰጠው ትርጉም አንድ አይደለም። ለምሳሌ በቀይ ሽብር የደርግ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው ፖለቲከኛ ሆነ ስንል በአብዛኛው ፖለቲከኞች የሚያደርጉትን እኩይ ተግባር የሚተገብር፣ እግዚአብሄር የለም የሚል፣ የሚገድል፣ ተንኮለኛ ሰው ሆነ ማለት ነው የሚል እይታ ይጣመረዋል። በዚህም ዘመንም የመንግስት ፖለቲከኛ ሆነ ስንል ዘረኛ ሆነ፣ ተንኮለኛ ሆነ፣ ሙሰኛ ሆነ የሚል ትርጉም ይዛመደዋል። በአብዛኛው ሰው አመለካከት ክርስትያን በሃገር አመራር ውስጥ መሳተፉ በበጎ አይታይለትም። ከዚህም የተነሳ አማኝ ክርስትያን ፖለቲከኛ ሊሆን አይችልም የሚል የተሳሳተ መረዳት አለ።
ሌላው ክርስትያን ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? እንደምታውቁት እኛ አገር አንድ ሰው ክርስትያን ሆነ ስንል የሰጠነው የራሳችን ትርጉም አለን። ዳግም የተወለደ፣ የሚጸልይ፣ ቤተክርስትያን የሚሄድ፣ የተጠመቀ፣ ጌታን የተቀበለ በማለት የራሳችን ትርጉም ሰጥተነዋል። ከተወሰነ ዓመታት በፊት ክርስትያን ሆነ ሲባል ዋጋ ከፍሎ የመጣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆነ እውነተኛ ክርስትናን በኑሮው የሚተገብር ታማኝ ማለት ነበር። እነዚህን ሁለት ቃላት በትክክል ከፈታን ክርስትያን ፖለቲከኛ ሊሆን ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ መነሳት የሚገባው አይሆንም።
በአሁን ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ከምንጊዜውም በበለጠ የወንጌል ዓማኞች በፖለቲካ ውስጥ ገብተው በሃላፊነት ቦታ ተቀምጠው የሚያስተዳድሩበት ጊዜ ነው። በአገራችን ታሪክ የወንጌል ዓማኞች በዚህ ቁጥር ከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ላይ ወጥተው አያውቁም። ግን ትልቁ ጥያቄ እነዚህ ሰዎች ተመላላሽ የዘመኑ ክርስትያኖች ናቸው ወይስ በእርግጥ የክርስቶስ ደቀመዝሙር ናቸው የሚለው ነው። ምክንያቱም ይህን ያህል ክርስትያኖች በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ገብተው ሳለ ለምን አገራችን እንደዚህ አይነት አሳሳቢ፣ የተበላሸና በዓለም ማህበረሰብ ፊት መሳቅያ የሆንበት ሁኔታ ላይ የደረስችው የሚለው ጥያቄ ነው በማለት ወደ ፖለቲካ ውስጥ መግባት ሳይሆን ዋናው ጥያቄ በገቡበት ፖለቲካ ውስጥ ጨው ሆነው አለመገኘታቸው ነው በማለት ክርስትያኖችን በፖለቲካ ከመሳተፍ የሚያግዳቸው የለም ሆኖም ግን ክርስትያን ሳይለወጥ ወደ ፖለቲካ እንዳይገባ በማለት በማስጠንቀቅያ ጭምር ጥያቄውን መልሶልናል።
ጽናት(Tsinat.com) በሚለው የቤተክርስትያን ጥራት መመዘኛ ሚንስትሪ የሚያገለግለው ወንድም ዶ/ር አዳም ቱሉ ደግሞ ፖለቲካን እንደ ሞያ እንደሚያየው እና ማንኛውም ሰው በሙያው ተምሮ እንደሚሰራው ሙያ ክርስትያኖችም በፖለቲካ ሙያ መሰማራት እና ፖለቲከኛ መሆን ይችላሉ በማለት የእኛ ማህበረ ክርስትያን በአገርና በወገን ጉዳይ ባለው ፖሊቲካ ላይ ያለው አመለካከት የተዛባና መስተካከል የሚያስፈልገው ነው ይለናል። በመቀጠልም የክርስትና ትምህርት በዘረኝነትና በጭቆና ላይ ፍርድ የያዘ መልእክት የአለው በመሆኑ ክፋትንና ኢፍትሃዊነትን በተገኘበት ቦታ ሁሉ ማውገዝ አለብን። ይህ አቋም በአለም ያሉ አብያተ ክርስትያናት የሎዛ ጉባኤ በተባለው ስብሰባ ላይ ተስማምተው ያጸደቁት የጋራ አቋም ነው። ፖለቲካ በክርስትያኑ ዘንድና ቤተክርስትያን ውስጥ የተፈራበትን ዋናው ምክንያትን ሲያብራራው በዘመናት መሃከል ቤተክርስትያን ወደ ፖለቲካ ጽንፍ ውስጥ በመግባት ከመንግስት ጋር በመተባበር የክፉ ስራ መጠቀምያ ስለሆነች ነው በማለት ከታሪክ በመነሳት ያስቀምጠዋል። ሁለተኛው ምክንያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች አውዱን ጠብቀን በመፍታት ካለመረዳታችን የተነሳ ሲሆን በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ሰብአዊነትና ፖለቲካን ስለ አቀላቀልነው ነው በማለት ዶ/ር አዳም ይገልጸዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የደጉ ሳምራዊን ክፍል ስንመለከት ፖለቲካ ሳይሆን ሰብአዊነት መሆኑን እናያለን። ክርስትያኖች ይህንን ነው ዛሬ ጊዜ ፖለቲካ ነው እያልን እየተውነው ያለነው። ድርሻችን ከመጸለይ ባለፈ ማህበራዊ ተሳትፎ እጅጉን ሊኖረው ይገባል እላለሁ በማለት ያጠቃልለዋል።
ጌታ እንዲህ ሲል አስታወቀን “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፣ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ሰዎች መብራት አብርተው ከዕንቅብ በታች አያስቀምጡትም ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ ” እኛን ጨው ሲለን፣ዓለም ሁሉ ጣም አልባ ጤና አልባ መሆኑን ሲነግረን ነው፣ እናንተ ብርሃን ናችሁ ሲለን ደግሞ ምድር ዓለም በጨለማ ዳንኪራ የሚረገጥበት አሳዛኝ ተውኔት እንደሆነ ሲያሳየን ነው። የጨው አብነቱ ደግሞ ወጥ ውስጥ መከተቱ ነው።የጨው አብነቱ ሲከተት ለውጥ ማምጣቱ ነው። ብርቱ ጥያቄዎች ቀርተውልናል። አንደኛው ወጡ ውስጥ ገብተናል ወይ? የሚል ነው – ዳር ቆመን ለመታዘብ፣ አፋፍ ላይ ሆነን አቃቂር ለማውጣት አልተጠራንም። እሳቱ እየተፋፋመ ሲቀጣጠል እያዩ አስተያየት ሰጪዎችና የጎዳና ተቺዎች በበዙበት ዘበናይ ዓለም ውስጥ የእኛ ጥሪ የእሳት አደጋ ሠራተኛነት ነው። ጥድፊያችን እሳት ማጥፊያ ውሃና መድሃኒት መርጨት ነው። የእሳቱን ትኩሳት እምብርት ፈልጎ ማውደም ነው። ትስጉት ብርቱ እንቅስቃሴ ነው። ከታዛቢነት ወደ ታዳጊነት፣ከርቀት ወደ ቅርበት፣ ከቦዘን ወደ ትጋት፣ ከፍዘት ወደ ትኩረት መሸጋገር ነው። እኛ IMPACT ለማምጣት፣ለአስሚነት ተጠርተናል። ያላሰማን እንደሆን እንደጌታችን ብያኔ ወደ ውጪ ተጥለን መረገጥ ይሻለናል። የክርስትያኑ ህዝብ በዚህ ኅብረተሰብ መኖር ፋይዳው ለውጥ ማምጣት ነው በማለት ከዚህ ያነሰ ኑሮ የዚህን አለም ሲቃ የሚያባብስ ራስ ገዳይ ዐላማ ቀልባሽ እንክርት ኑሮ ነው በማለት መስተዓየት በሚለው መጣጥፉ ውስጥ ወንድም ንጉሴ ቡልቻ ይመክረናል።
በተስፋ ዐቅበተ እምነት(apologitics)አገልግሎት የነገረ መለኮት ሊቅና አስተማሪው ዶ/ር ተስፋዬ ሮበሌ “ክርስቲያንና ፖለቲካ ፦ አቋም የለሹ አቋማችን” በሚለው ጽሁፉ ”በየዘመናቱ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስ ሰጠኝ የምትለውን ዐደራ ከዳር ለማድረስ፣ በሚያስፈልገው ሁሉ በመውተርተር ላይ ትገኛለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ነዳያንን በማብላት፣ የታመሙትን በማስታመም፣ ለመበለቶች ዳኛ በመሆን ጥልቅ ስም አላት፡፡ በርግጥም ቤተ ክርስቲያን የምስካየ ሕዙናን መንበር ናት፡፡ ወደ ፊትም ይህንኑ ግብረ ሠናይ ምግባሯን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን ችግሩን በዘላቂነት መፍታት የም ትችለው የተሳሳተ ፖሊሲ ያስከተለውን ፍሬ በመልቀም ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥት ትክክለኛ ፖሊሲ እንዲነድፍ ስታስተምር፣ መንግሥት ሲሳሳትም ስሕተቱን ስሕተት ነው ማለት ድፍረትና ክህሎት ሲኖራት ብቻ ነው፡፡“አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ መስሎ ለመኖር ብቻ ውሃና ዘይትን ካለዋሃድን፣ እሳትና ጭድን ከላፋቀርን፣ ዐይንና ናጫን ከላስማማን የሚል አቋም ያላቸው ይመስላል፡፡ እውነትን ከጥቃት የምንጠብቀው ሐሰትን በግልጥ በመቃወም ጭምር ነው፡፡
መቼም መንግሥት ከእርሱ ተቃራኒ ዘዌ የቆሙትን ሁሉ “ጸረ” የሚል የመነሻ ምዕላድ እየቀጸለ፣ ጽንፍ የነካ በመሰለበት በዚህ የታሪክ ጊዜ፣ መለሳለስ ጥሩ ስልት መስሎ ሊታይ ይችል ይሆናል፡፡ ግን የክርስቶስ ወንጌል የጀግኖች መለዮ እንጂ፣ የአልጮች ሙያ አይደለምና ልፍስፍስ አቋማቸውን መቀየር የግድ ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ነው አንድ ወንድማችን ይህን አስመልክቶ፣ “አቋም የለሽ አቋማችን” እንዲስተካከል በአንድ ጽሑፉ የሚማጠነን፡፡ እውነት ነው አቋም የለሽ አቋማችንን እክ እንትፍ እንበለው፡፡ የአቋም ሰው መሆን ያስከብር ከሆነ እንጂ አያዋርድም (ቢያንስ በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት) በማለት ይመክራል፡፡
በማርች 2017 በስፕሪንግፊልድ ቨርጅንያ “ ክርስትያንና ፖለቲካ ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን የፓነል ስብሰባ አዘጋጅና ተሳታፊ የነበረው ወንድም ኮነ ፍሥሐ ለጠየቅነው ሲመልስልን:- ቤተክርስትያን ዋና ተልዕኮዋ ወንጌልን ለፍጥረት ማዳረስ ቢሆንም በፖለቲካው ዓለም ደግሞ የመንግሥት ጌታም ሆነ ባርያ ሳትሆን ሕሊናው በመሆኗ ልትወቅሰው እና መንግስትን ተመለስ ልትለው ይገባል። ይህንን ድርሻ ሁሉም ቤተ እምነቶች ሊተገብሩት የሚገባ እውነታ ነው። ስለዚህ የጽድቅን አቅጣጫ አመልካችና መንግስት ሲሳሳት ደግሞ ወቃሽ እንጂ የመንግሥት መሣሪያና ድምጹን የምታስተጋባ ካድሬ ልትሆን በጭራሽ አይገባም። የክርስትያን ፖለቲካ ከእውነት ጋር በመወገን ለድሆች መቆምን ይጠይቃል። በዚህ ዘመን የምናያቸው የመድረክ ዝምታዎችና ልማታዊ ስብከቶች ሚዛን የደፉ የክርስትያን አስተምህሮ አይመስሉም። ድሃው ህዝብ ቆሻሻ እየተደረመሰ ሲገድለውና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን በረሃብ ጫፍ ላይ ተንጠልጥለው ባሉበት ዘመን ሰዐታት በመቆም ጸሎት እና ጾም እንጂ ሃገር ሰላም ነው በማለት ከሽብሸባ አልፈን ወደ ዳንስና ረገዳ መሸጋገራችን ርቱእ ከሆነው ነባራዊ የፖለቲካ ርዕዮት ብዙ እንደራቅን ያሳያል።
በመቀጠልም ቤተክርስትያን የክርስቶስ ስለሆነች የምትገዛበትም ላዕላይ መተዳደርያ የእግዚአብሄር ቃል መሆን አለበት። ቤተክርስቲያን በሐዋርያት ዘመን የነበራትን ፊት ለፊት፣ ሳትፈራ፣ በድፍረት የመገሰጽ ክህሎት በዚህ ዘመን ካልተገበረች አንዳች የማትፈይድ ግብረገባዊም ሆነ መንፈሳዊ ሥልጣን የሌላት፡ ሙት ሃይማኖታዊነት የረበበባት የማሕበረሰብ መሰብሰቢያ ሆና ልትቀር ትችላለች። ፖለቲካን በጽንፈኝነት መመልከቱ ቤተክርስትያንን ወደዚህ አደጋ ሊዳርጋት ስለሚችል ሚዛናዊ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል።
ሌላው ለመንግስት መገዛት የሚለውን ቃል የምንፈታበት ስሁት አመለካከት ነው። ክርስትያኖች ለመንግስት ተገዙ የሚለውን ቃል መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዛቸውን ሌሎች መገዛቶች በሚያዩበት ዐውደገብነት(contextualization) ልክ እንጂ ለመንግስት ተገዙ የሚለውን ከልኩ በላይ አካብደው በውግዙም በስሁቱም ለመንግስት አጎብዳጅ ፖለቲከኛ ከመሆን መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ክርስትያኖች ለመንግስት አሜን ብለን የምንገዛው ከእግዚአብሄር ቃል ጋር የማይጋጭ ሲሆን ብቻ ነው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ “ሚስቶች ሆይ ለባሎች ተገዙ” ሲል ሚስቱ ለባልዋ በመገዛት የወንጀል ተባባሪው ትሁን ማለት አይደለም። እንደ እግዚአብሄር ቃል ባልሆነው ምክር ላይ የባልዋን ስሁት ጥያቄ እንቢ! ልክ አይደለህም፣ ተመለስ! ብላ መገሰጽ ወይም አለመተባበር ይጠበቅባታል። መጽሐፍ ቅዱስ ለመንግስት ተገዙ ሲል የተጠቀመው ቃል ተመሳሳይ ሲሆን ዐውደገብ አፈታቱም አንድ አይነት ነው። እንደ እግዚአብሄር ቃል ያልሆኑ የመንግስት ትዕዛዞችን ልክ አይደሉም በማለት በድምጽም ይሁን ባለመተግበር መቆም እውነተኛ የክርስትያን ፖለቲካ ነው። ድፍረት ከሌለን ጥራዝ ጠለቅ እስክንሆን ድረስ ወደ ፖለቲካ አለመግባቱ ይሻላል እላለሁ በማለት ጠንካራ ምላሽ አስቀምጦልናል።
ማጠቃለያ
ጻድቅ የሃገር ስልጣን በሚይዝበት ጊዜ ለሃገር መልካምና ብልጽግና እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ስለዚህ ለሃገራችን ተስፋዋ እውነትን የያዙ፣ የእግዚአብሄርን መንግስት ያወቁ፣ በዘረኝነት የማይጠላለፉ፣ ሙስናን የሚጠየፉ፣ ለደሃው የሚያዝኑ፣ በሚሄዱበት ለእውነትና ለፍትህ የሚቆሙ ክርስትያኖች በመንግስት አስተዳደር ስልት ወይንም በፖለቲካው ተሳትፈው ተጽእኖ መፍጠር ሲችሉ ነው ብለን እናምናለን። ስለዚህ ትውልድ የሚገደን ክርስትያኖች ልናደርግ የሚገባንና ልናስተላልፍ የሚገባን መልዕክት አለ። ከላይ ወንጌላዊ ያሬድ እንደገለጸው ዘመነኛው ንፋስ እያራገበ ያለቦታው ያስቀመጠውን ስመ ክርስትያን ፖለቲከኛ መዝኖ መለየትና ተስተካከል ማለት መቻል አለብን። የከበረውን ከተዋረደው እየለየን ለሁሉም ልክልኩን ማስቀመጥ አንዱ ትልቁ ሥራችን ሊሆን ይገባል። በስልጡን እሳታዊ ምላስ ተደግፎ ዘሎ ፖለቲካ ከመግባት በፊት ህይወትን መዝኖ ከእውነት ጋር የምቆም ደቀ መዝሙር ነኝ ወይ? ብሎ መጠየቅ ግድ ይልዋል። ያንጊዜ እኛም እሰየው እንኳን ለዚህ አበቃህ እንደ ቃሉ “ለድሃ አደጉ የሚሟገት፣ ሊታረዱ የተፈረደባቸውን የሚታደግ” ተነሳልን ብለን ደስ ይለናል። ታሪክም እንደ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልትን በድንጋይ ሲያቆምላቸው ቀላያት ደግሞ በሕይወት መዝገብ ላይ በሚሰፍረው ስማቸው ሃሴትን ያደርጋሉ።
ኮነ ፍሥሐ፣ ከስፕሪንግፊልድ፣ ቨርጂንያ