ሕይወት ቢመሰክር – ከወንድም ኮነ ፍሥሐ

የተሰጠህን በረከት ለራስህ ብቻ ቀብረህ ይዘኸው ይሆን? ለእግዚአብሔር በመታዘዝ ይህን በረከት ለሌሎች ማፍሰስን ካላወቅህ ፣ ሌሎች የእግዚአብሔርን ማንነት በሕይወትህ ማየት አይችሉም።”ለ ክርስቶስ መጠላትን በትንሹ ለመቅመስ በሰሜን አሜሪካ ጎዳናዎች ላይ ለምስክርነት መውጣት በቂ ነው። በጥቂት ሰዓት ውስጥ ጥላቻ፣ ስድብና ግልምጫ ይፈራረቁባችኋል:: አላዋቂ ሁዋላቀር ትባላላችሁ፡፡ በዚያው መጠን ደግሞ ከባህር ማዶ መጥታችሁ ወንጌልን በአደባባይ መመስከራችሁ ከብዙዎች አድናቆትን እና ፈገግታን ያተርፍላችኋል:: ሆኖም ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ወደ ኋላ አፈግፍገው ወደ ተዉት ወደዚህ ጥሪ ከመሰማራትዎ በፊት፤ ስራው ባለቤት እንዳለውና ባለቤቱ ማን እንደሆነ ተረድተው፤ በቃሉ እውቀት እንዲታጠቁና ጸጋው እንዲበዛልዎት ጸልየው፣ ከዚህም በላይ ለስራው ባለቤት ለመታዘዝ ፈቃደኛ መሆንዎን ማረጋገጥ የማይታለፍ ዋነኛ ጉዳይ ነው። የዚህ ጽሁፍ ዓላማ በመለኮታዊ ምሪትና በጽናት ጎዳና ስለተጓዙ መስካሪዎች ሕይወት መናገር ቢሆንም፣ ወደዛ ደረጃ ለመድረስ ያለውን ተግዳሮት ማንሳቱና ስህተቱን መንቀሱ በዛ ያለውን ድርሻ ይዟል። የወንጌል ምስክርነት ዋናው ቁልፍ ኃይልን በሚሰጠው በክርስቶስ ተደግፎ የማዳኑን ጸጋ ለሌሎች ማድረስ ነው። መታዘዙ የእኛ ድርሻ ሲሆን የውጤቱ ጉዳይ ደግሞ ሰዎችን ወደራሱ የሚጠራው የስራው ዓለቃ (የባለቤቱ) ሃላፊነት ነው። ሆኖም ለስራው ባለቤት መታዘዝና “በኅይሉ ችሎት” መደገፍ ካልቻልን ሰዎች ወንጌልን ላለመቀበላቸው የማይመስል ምክንያት እየሰጠን ዘመኑን መዋጀት ሲገባን፣ ችግር ተራኪ ጋዜጠኛ ሆነን እንቀራለን። በብዙ ወኔ ተሞልተውና በከፍተኛ ስሜት ተነሳስተው፤ ነገር ግን ብቻቸውን ወጥተው አንድም ሳይማርኩ የተመለሱ ብዙ ናቸው። ከጌታ ጋር አብረው ወጥተው ዘርን ዘርተው ሌላም ማርከው የሚመለሱም በርካቶች ናቸው። የሰዎችን ጆሮ እንጂ ልብ አለማግኘቱ አማሮት ከምስክርነት አገልግሎቱ ተለይቶ የነበረው የአሳዬ ገጠመኞች ለሁላችንም ትምህርት ይሰጡናል። የሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆነው አሳዬ በመጀመርያው የምስክርነት ዓመታት ሰዎችን መስክሮ ከማምጣት ይልቅ እንዲሸሹ ያደረገባቸውን ሁኔታዎች ሲያስብ በጣም ይገረማል። ከአስር ዓመታት በላይ ባስቆጠረው የክርስትና ጉዞው በመጀመርያዎቹ የሞቅታ ዓመታት ውስጥ ስንት ሰው ወደ ጌታ አመጣህ? ብትሉት፣ ካመጣሁት ይልቅ ያባረርኩት ይበልጣል ቢላችሁ ልትደነግጡ ወይም አማኝ መሆኑን ልትጠራጠሩ ትችላላችሁ። በነዚያ የክርስትናው የመጀመርያ ዓመታት የነበረው የመመስከር ፍላጎቱና ድፍረቱ ከፍተኛ ቢሆንም ፣ፍሬ ያልታየበት ነበር። የዚህም ምክንያቱ በቃሉ ብስለት ያልነበረውና በጸሎት ያልተደገፈ መሆኑ ነው። እርሱ በደንብ ያላወቀውን ጌታውን ለሌሎች ለማሳወቅ ሩጫ የጀመረው ጌታን በተቀበለ በወሩ ቢሆንም የስራውን ባለቤት ለምን ጠራኸኝ? ምን ልታዘዝ? ብሎ አልጠየቀም። ወደ ራሱ የጠራውን ጌታ ከተደበቀበት ፈልጎ ያገኘው ይመስል ለሌሎች ለማሳየት ቸኩሎ ነበር። አሳዬ ኢየሱስን “ጌታዬና አምላኬ” ብሎ እንደተቀበለው አላስተዋለም። በራሱ ኃይል ተደግፎ ነበር አገልግሎት የጀመረው። ሆኖም በውጤቱ ሰዎች እሱን እንዲመለከቱ አደረገ እንጂ ማንንም ወደ ጌታ አላመጣም። እስቲ ጥቂቶቹን የአሳዬን የየዋህነት ዘመንና የምስክርነት ገጠመኞች እንመልከት። ለአሳዬ የመጀመርያው ችግሩ ምስክርነቱ “ጌታ ከእንደዚህ አይነት ችግር ውስጥ አውጥቶ እንደዚህ አይነት ስኬት ላይ አደረሰኝ” በሚል ግለ ታሪክ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነበር። ብዙዎች ሰሚዎቹ “እንኩዋን ደስ ያለህ!” በሚል ምላሽ ያቆማሉ።

To Read the full Article on Berea Magazine 2016 click here